ለቅሶ በግዴታ!

(የጎንደር ዩኒቨርስቲ እና የወላይታ ህዝብ ሃዘን እንዲወጣ የተጠራባቸውን ደብዳቤዎች ይዘናል)

የንጉሥ ለቅሶ - በወላይታ።

(ኢ.ኤም.ኤፍ) የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ለቅሶ አስመልክቶ፤ በቅርቡ ተከታታይ ዘገባዎች ሲቀርቡ ነበር። ከነዚህም መካከል፤ በመንደር ውስጥ የሚገኙ እድሮች ሳይቀሩ ህዝቡ በግድ ለቅሶ እንዲወጣ ሲደረግ ነበር። በ እስር ላይ የሚገኙ ታራሚዎች እና የጎዳና ተዳዳሪዎች ጭምር ሃዘናቸውን ገልጸዋል። ይህንንም አስመልክቶ አቶ በረከት ስምኦን በተለይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ማመስገናቸው የሚታወስ ነው። በተለይም የጎዳና ተዳዳሪዎችም ሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች፤ የሚያለቅሱት ላለፉት 21 አመታት በኑሮ ውድነት ምክንያት ህይወታቸው እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ይሁን የጠቅላይ ሚንስትሩ ሞት በርግጥ አዝነው በውል አልለየም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለይ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር ሞት ሰምተው ለቅሶ ያልደረሱ እድርተኞች፤ እንደማንኛውም እድር ቅጣት ተፈጻሚ የሚደረግባቸው መሆኑ ታውቋል። በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች እና በዩኒቨርስቲዎች ጭምር ህዝቡ ለቅሶ እንዲወጣ ማሳሰቢያ እየተለጠፈ ነው። ከነዚህ ማሳሰቢያዎች መካከል ለጊዜው በእጃችን የገቡት የወላይታ እና የጎንደር ዩኒቨርስቲ ደብዳቤዎች ናቸው። በእለቱ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው፤ ሰራተኞች ስራቸውን አቁመው በጎንደር መስቀል አደባባይ እንዲገኙ ነው – ትዕዛዝ የተሰጠው። በወላይታ ሶዶ ከተማ የተጠራው ለቅሶ ደግሞ ከዚህ ለየት ያለ ነው። ደብዳቤው እንደገለጸው ህዝቡ በሶዶ ስቴድየም ተገኝቶ  ለአንድ ንጉሥ ሊደረግ በሚገባ ባህላዊ ለቅሶ እንዲደረግ ይጠይቃል። በዚህም መሰረት ሃላፊዎች የተቋማቸውን ማህበረሰብ በተደራጀ ሁኔታ እንዲገኙ አሳስቧል።

በሃዘኑ ምክንያት... ለግማሽ ቀን ስራም ሆነ ትምህርት አይኖርም።

እንዲህ ያሉ ደብዳቤዎች በተለይ በአዲስ አበባ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ በመጪው እሁድ ቀብር እንዲወጡ ታዘዋል። ይህም በየመስሪያ ቤቱ ቦርድ ላይ ተለጥፏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሃረር፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በወለጋ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በጅጅጋ እና በቤንሻንጉል አካባቢዎች ተመሳሳይ የሆነ የሃዘን ሰልፎች እምብዛም አልታየም። ከዚህ በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የመንግስት ሰራተኞች እና ነጋዴዎችም እንደሌላው በነቂስ ወጥተው እንባ ሲራጩ አልታዩም ነበር። አሁን ግን በግድ እንዲወጡ በመደረጉ ከዚህ በኋላ ሌሎች ክልሎችና የህብረተሰብ ክፍሎችም የሚቀጥለውን ሳምንት ቀብር ያዳምቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

(በአሁኑ ወቅት በየከተሞቹ የሚደረጉት ለቅሶዎች በህዝቡ ፍላጎት እንደሆነ ተደርጎ በሚዲያ እየተነገረ ነው። እውነታውን ሌላውም ህዝብ እንዲያውቀው፤ እንዲህ አይነት ደብዳቤዎችን በኢሜይል አድራሻችን media.emf@gmail.com በመላክ ይተባበሩን)

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on August 26, 2012. Filed under COMMENTARY,VIEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.