ለሚኮበልሉ የህወሃት/ኢህአዴግ ልዑካን በሙሉ፡-

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች እንወክለዋለን ያላችሁትን “መንግሥት” ዓላማ በማንገብ ስብሰባ ለማድረግ ስትሞክሩ እንደነበር በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ይህ 52 ግለሰቦችን ያካተተው ቡድን ባሳለፍነው የሳምንት መጨረሻ በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን ለማከናወን ሲንቀሳቀስ በየከተማው የደረሰበትን ከፍተኛና ጠንካራ ተቃውሞ ከማንም በላቀ መልኩ የተመለከታችሁና በቅርበት የተከታተላችሁት እናንተ ናችሁ፡፡ በውጪ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብቱ የተከበረ በመሆኑ ይህንን ዓይነት ተቃውሞ አቀረበባችሁ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ወገናችን ከዚህ ዕድል ጥቂቱን ቢያገኝ ሊያሰማችሁ የሚችለውን ተቃውሞና ተግዳሮት ምን ያህል ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያቅታችሁም፡፡ የ1997 ምርጫና ለውጥ የናፈቀው ታሪካዊው “የሕዝብ ሱናሚ” የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች በመሆናቸው በዚያን ወቅት የታየውን የሕዝባችንን ግልጽ ተቃውሞ የምትዘነጉት አይመስለንም፡፡

በአገራችን ውስጥ ላለፉት 20 ዓመታት የተካሄደው የመብት ረገጣ፣ ጭቆና፣ አፈና፣ ግድያ፣ ወዘተ አሁንም የቀጠለ በመሆኑ ይህ ደግሞ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቀጣይነት እንዲኖረው እያደረጋችሁ ያላችሁት እናንተ መሆናችሁ አትዘነጉትም፡፡ የሥርዓቱ ደጋፊና አቀንቃኝ በመሆን እስካሁን ያደረጋችሁት አገር ቤት ያለው ሕዝባችንም ይሁን እኛ በውጪ የምንገኝ ጠንቅቀን የምናውቀው ነው፡፡ እንዲሁም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ወደፊት በማስረጃነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሰነዶች በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን የሰበሰበ መሆኑንና አሁንም ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ በተቀናጀ መልኩ በእያንዳንዱ በኃላፊነት ላይ በተቀመጠ ግለሰብ ላይ እየሰበሰበ መሆኑን ልናሳውቃችሁ እንወዳለን፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን ሰላም፣ እኩልነት፣ አንድነትና ዕርቅ የሰፈነባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመመሥረት የሚታገል እንደመሆኑ መጠን የዚያኑ ያህል ደግሞ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብና መረጃዎችን በመሰብሰብ በኩል አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል፡፡ ስለዚህ በቅርቡ ይህ በአገራችን ላይ የሚካሄደው ግፍ ማቆሚያ በሚደረግለት ጊዜ የእናንተና የመሰል ጓደኞቻችሁ መጻዒ ዕድል ምን እንደሚሆን መገመት የሚያቅታችሁ አይመስለንም፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንደምንሰማውም ሆነ አንዳንዶች በግልጽ ለጋራ ንቅናቄያችን እንደሚነግሩን በኢህአዴግ ውስጥ በአባልነት የተመዘገቡ የሥርዓቱ አራማጆች የሚፈጽሙት ተግባር በሙሉ አምነውበት እንዳልሆነ ነገር ግን የእንጀራ ጉዳይ በመሆኑ ወይም አማራጭ ከማጣት የተነሳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከእናንተም ውስጥ ከዚህ ጎራ የምትሰለፉ ጥቂቶች እንዳልሆናችሁ እናምናለን፡፡ መውጫ መፈለግ ተገቢ ነገር ቢሆንም መውጫውን ማግኘቱ ደግሞ አስፈላጊም ነው፡፡ ስለዚህም ነው ይህንን ዕድል እንድትጠቀሙበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ልናሳስባችሁ የምንወደው፡፡ እስካሁን የፈጸማችሁትን ስህተት መሰረዝ አይቻልም – ጊዜው አልፏልና፡፡ ከዚህ ወዲያ ያለው ግን በእጃችሁ ያለ በመሆኑ አሁን የሚሰጣችሁን ዕድል ሳትጠቀሙበት ቀርታችሁ ወደቀድሞው ሥራችሁ በመመለስ ሕዝባችንን ለመበደል የምታደርጉት ቀጣይ ሥራ በዕርቅ ብቻ ለማለፍ የሚያስቸግር ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ነው የጋራ ንቅናቄያችን ይህንን ዕድል ተጠቅማችሁ አሁን ማቆሚያ እንድታበጁለት ጥሪ የሚያደርግላችሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስትመለሱ ሳይሆን እዚሁ እያላችሁ ይህንን የተቀደሰ ውሳኔ በማድረግ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ እና አንድነት የሚሰፍንባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት የሚደረገውን ትግል ዛሬ ለመቀላቀል ውሳኔ አድርጉ፡፡

በመሠረቱ አኢጋን የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ከየትኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር የወገነ ባለመሆኑ ነገር ግን “ከዘር ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጥባት” አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት የሚታገል በመሆኑ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በዕኩልነት መነጽር የሚያይ ስለሆነ እናንተንም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለይቶ የሚያይበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡ ከጋራ ንቅናቄያችን መሠረታዊ መርሆዎች መካከል አንዱ በአገራችን ዘላቂነት ያለው ዕርቅ መስፈን እንደመሆኑ ለዚህ ተግባር ራሳችሁን በመስጠት እየሞተ ያለውን አገዛዝ ትታችሁ ለራሳችሁና ለሌሎች ነጻነት በአንድነት መታገል እንድትችሉ ነው ይህንን ጥሪ የምናቀርብላችሁ፡፡

በተለይ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ በተለያዩ የሰሜንና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች እየተካሄደ ባለበት ወቅት ይህ ለውጥ ወደአገራችን መዛመቱ የማይቅር እየሆነ የመጣ ሃቅ ነው፡፡ ጥያቄው ይህ አሁን የተሰጣችሁን ዕድል ንቃችሁ ለውጡ እውን በሚሆንበት ጊዜ ሕዝቡ ከያላችሁበት እያደነ ሲያወጣችሁና ያላሰባችሁትና ያልጠበቃችሁት በሙሉ ሲከሰት “እኛ እኮ ሕዝቡን ለማስተዳደር ኮንትራት የፈጸምን መስሎን ነበር?” ልትሉ ነው ወይስ የተለመደችውን “እኔ እኮ ትዕዛዝ ፈጻሚ ነኝ፤ የታዘዝኩትን ነውን’ጂ የፈጸምኩት ምንም ያደረኩት ነገር የለም“ ልትሉ ነው? በአገራችን ንጉሣዊው ሥርዓት እንዲሁም የደርግ አገዛዝ በወደቁበት ጊዜ የሆነውን መለስ ብሎ ማሰቡ ትልቅ ትምህርት የሚሰጣችሁ ይመስለናል፡፡ አንድ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ነገር “ታሪክ ራሱ ይደግማል ከዚያ የማይማሩ ግን ደንቆሮዎች ናቸው“ የሚለው አባባል እውን እንደሚሆን ሲሆን እናንተ ግን ከታሪክ ተምራችሁ ተገቢውን ውሳኔ የማድረግ ቁርጥ እርምጃ እንደምትወስዱ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ለ40 ዓመታት የጋዳፊን ሥርዓት ሲደግፉና ሲያራምዱ የነበሩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጊዜያቸው በደረሰ ጊዜ ከሕዝባቸው ጋር እንደቆሙ ሁሉ እናንተም ውስጥ እንዲህ ያለው ከሕዝብ ጋር አብሮ የመሰለፍ ፍላጎት ዳብሮ ፍሬ የሚያፈራበት ወቅት አሁን በመሆኑ ዛሬ ውሳኔያችሁን እንድታደርጉና “ከእንግዲህስ በቃ“ በማለት ራሳችሁን ነጻ አውጥታችሁ የእናንተን አርአያ ለመከተል ለሚሹ ሁሉ ፋና ወጊ እንድትሆኑ በጥብቅ ልናሳስባችሁ እንወዳለን፡፡ በአገራችን “ስም ከመቃብር በላይ ይውላል“ እንደሚባለው ዛሬ ይህንን ውሳኔ ብታደርጉ በታሪካችሁ ላይ የሚዘከረው እስካሁን ያደረጋችሁት ብቻ ሳይሆን ከዚህ በኋላ የምታደርጉት በመሆኑ ለራሳችሁ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችሁና ለቀሪው ዘራችሁ በማሰብ ይህንን ቁርጥ ውሳኔ የምታደርጉበት ጊዜ አሁን ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የምናስተላልፈው መልዕክት ቢኖር እነዚህ ግለሰቦች ወደእኛ ለመምጣት ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ እነርሱን ለመቀበል የቅድሚያ ዝግጅት እናድርግ፡፡ ከስሜት እና ከደመኝነት ባለፈ መንፈስ ጉዳዩን እንመልከተው፡፡ ለአገራችን የሚበጃትን በሰከነ ሁኔታ በማሰብ ለዘላቂ ሰላምና ዕርቅ ራሳችሁን እንድታዘጋጁ የጋራ ንቅናቄያችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በመጨረሻም እናንተ በዚህ የልዑካን ቡድን ውስጥ የምትገኙ በሙሉ ይህንን ጥሪ ተቀብላችሁ ከብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ጋር ለመቀላቀል ውሳኔ በምታደርጉበት በማንኛውም ጊዜ ከጋራ ንቅናቄያችን ጋር በስልክም ሆነ በኢሜይል ልትገናኙ እንደምትችሉ በግልጽ እናሳውቃለን፡፡ ከዚህ ሌላ አሁን ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ አገዛዙ የሚወገድበትን መንገድ በህቡዕ ለመሥራትና እንቅስቃሴውንም ከውስጥ ሆኖ ለመደገፍ የምትፈልጉ ከእናንተ መካከል እንዳላችሁ የማይካድ ሃቅ በመሆኑ ይህንን ሥራችሁን እንድትቀጥሉና ከጋራ ንቅናቄያችን ጋር የዘወትር ግንኙነታችሁን በመቀጠል መረጃ በማቀበልም ሆነ ሌሎች ምስጢራዊ ሥራዎችን የመሥራት ተግባራችሁን እንድትገፉበት እናሳስባለን፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ይህንን ጥሪ እምቢ በማለት የማንአለብኝነት ተግባራችሁን ለመቀጠል የምትወስኑ ሁሉ በተገቢው ጊዜ ለፍርድ የምትቀርቡ ብቻ ሳይሆን ይህ ጥሪ ራሱ ለእምቢተኝነታችሁና ጸረ-ሰላም ለመሆናችሁ ማስረጃ ሆኖ የሚቀርብባችሁ መሆኑን እንድታውቁት በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

ፈጣሪ አገራችንን ይባርክ፤ ለእናንተም ድፍረቱና ልቦናውን ይስጣችሁ፡፡

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)

***********************************************
ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ዋና ዳይሬክተሩን ለአቶ ኦባንግ ሜቶ (obang@solidaritymovement.org) በመጻፍ
ወይም በስልክ (202) 725 – 1616 በመደወል ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 14, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.