ለመስከረም 3 ሰልፍ ጋባዣችን ህሊናችን ነው

[PDF] መስከረም 3 ቀን 2002 ዓ.ም. (September 13 2009) በዋሽንግተን ዲ.ሲ. በዋይት ሐውስ ፊት ለፊት 100ሺህ እድምተኛ የሚጠበቅበት እና ወያኔ በሕዝባችን ላይ የፈጸማቸውንና በመፈፀም ላይ ያለውን በደል፣ ስቃይ፣ ግድያና እስራት ለማጋለጥ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የሚወዱ ሁሉ ሊገኙበት የሚገባ ታላቅ ሰልፍ የሚደረግበት ቀን ነው። 

በዚህ ሰልፍ ላይ ለመገኘት ማን ነው የጠራው ብሎ መጠየቅ እንኳን የሚገባ አይመስለኝም፡ ማን ነው የጋበዘኝም ወይም የሚጋብዘኝ ብሎ መጠየቅም አስፈላጊ አይደለም። ጋባዣችን የራሳችን ሕሊና ነው፡ በሐገራችን የሚደረገው የሰብኣዊ መብት ጥሰት፣ የሕዝቦች መንገላታት፡ መታሰር፡ መሰቃየት የሚያንገበግበን ሁሉ በተለይም በዋሽንግተን ዲሲ እና በአካባቢዋ ነዋሪዎች የሆንን ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሞትና የሕይወት፣ የመኖርና ያለመኖር ውሳኔ መሆኑን ተገንዝበን፣ ይሕ ሰልፍ ለሐገራችን ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ እንኳን አናሳ ቢሆን ነገር ግን ከሕሊና ወቀሳ እራስን ለማዳን ካለን የስራና ሌሎችም ግዴታዎች ይህችን ግማሽ ቀን ለዚህ ታላቅ አላማ ለማዋል መዘጋጀት ይኖርብናል።

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ የሆነች የምትገርም ነገር ብሎ በጆሮዬ ሹክ አለኝ። አንዳንድ ያውም የፓርቲ መሪዎች ነን የሚሉ በዚሕ ሰልፍ ላይ አንገኝም ሲሉ ተደምጠዋል አሉ ብሎ ነበር የነገረኝ። ይህችን ነገር ግን አንድ ቀን ማታ ፓልቶክ ክፍል ገብቼ ሳዳምጥ አንድ በጣም ጥሩ ተናጋሪ ‘እንዴት እዚህ ሰልፍ ላይ አትገኙ ብሎ ያውም ወያኔን ተቃዋሚ ነን በሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች እንደዚህ አይነት ቅስቀሳ ይደረጋል’ ሲል በጆሮዬ ጥልቅ ሲል ሰምቻለሁ። በእውነት ይህንን ያሉ ወይም ለመቀስቀስ የተነሱ ካሉ የኢትዮጵያን መነሳት ሳይሆን በእውነት ውድቀቷን የሚመኙ ለመሆናቸው ምንም ማስረጃ የሚያሻን አይደለም።

እነዚህ ፓርቲዎች ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ብለው ለመጥራት የሚዳዱ ከሆነ ወይንም እውነት ለሐገራችንና ለሕዝቧ ነው የምንታገለው የሚሉ ከሆነ ከዚህ ሰልፍ ላይ መገኘት የበለጠ ፓርቲያቸውንም ትግላቸውንም የሚያሳውቁበት መድረክ ሊያረጉት ይችላሉ። ብሎም ደግሞ ከሌሎች የትግል አጋሮቻቸው ጋር በመገናኘት እንደውም ወደፊት በበለጠ አብረው ሊሰሩ በሚችሉበት ሁኔታዎች ለመመካከር እንዲረዳ መተዋወቂያም መድረክ ሊሆን ይችላል።

ይህ ሰልፍ የተጠራው ግለሰቦችን ለማሳወቅ እና ለማግነን አይደለም፡ መረዳት የሚኖርብን አንድ ነገር ቢኖር ግለሰቦች ለሐገርና ለወገን ቀንና ሌሊት ያለእረፍት ቀና በማሰብ በሚሰሩት ጥሩ ሥራና ተግባር ታዋቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ሌሎቻችን ለምን ተበለጥኩ በሚል መጥፎ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ በመነሳሳት መልካም ሥራቸውን ከማጉደፍና እነሱንም ብዙ ጠቃሚ ሥራዎችን ሊሰሩ ሲችሉ ከማስተጓጎል እንድንቆጠብ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻናል። ለመሥራት ችሎታውና ዕውቀቱ ካለን ብዙ የሚሰሩ ሥራዎች አሉና መላውን በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በማስተባበር ሁላችንም ድርሻችንን ልንወጣ ያስፈልገናል። ለዚህም ቅን ልቦና ጥሩ ህሊና ያስፈልጋል።

ሰልፉ የተጠራው በሐገራችን በኢትዮጵያ ያለውን ኢ-ፍትሀዊ የሆነ መንግሥት ለማጋለጥና በአሜሪካ መንግሥት የሚደረግለትን ማንኛውንም እርዳታ ለሕዝቡ ከሚሰጣቸው የዲሞክራሲ መብቶች ጋር በማያያዝ እርዳታው የግለሰቦችን ኪስ ማደለቢያ እንዳይሆን ለማሳወቅ ነው። ሕዝባችን የዚህ እርዳታ ዋንኛ ተጠቃሚ በመሆን በልቶ የሚያድርበትንና ብሎም ራሱን ችሎ ከተመጽዋችነት የሚወጣበትን ጊዜ ለማሳጠር የሚረዳን አጋጣሚ ነው።

ከሁሉም በላይ ይህ ሰልፍ በኢትዮጵያ ያለአግባብ ሰብዓዊ መብታቸው ተገፎ በእስር የሚማቅቁትን የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ የሚጠይቅና የፕሬዚደንት ኦባማ አስተዳደር በዚሁ ላይ ግፊት እንዲያደርግ የሚጠይቅ ነው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እዚህ ላይ በአብነት ማንሳት ይቻላል። የሷንና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች መፈታት የሚሹ ሁሉ ተገኝተው ድምፃቸውን ማሰማት ይጠበቅባቸዋል።

ይህ ሰልፍ ኢትዮጵያውያን በሐገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረው የመናገር የመሰብሰብ ሌሎችም ሌሎችም መብቶቻቸው ተገፈው በአሁኑ ሰዓት ከሐገር ውጭ ለስደት የሚዳረጉት ብዛት ያለው ሕዝባችን በተለያዩ ሐገሮች የሚደርስባቸው ግፍና ሰቆቃ ያበቃ ዘንድ ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ ነው።

ይህ ሰልፍ ኢትዮጵያውያን መታወቂያችን የሆነውን የሕዝባችን በረሐብ አለንጋ መገረፍ የሚያበቃበትና በሐገራችን ብሔራዊ እርቅ ተደርጎ ሁሉም የተማረ ዜጋ ሁሉ በአንድነት ለሐገር ብልፅግናና እድገት በመሥራት ድሕነትን ለማጥፋት ሁሉም እንዲነሳ ዜጎች ትብብራቸውን የሚያሳዩበት ነው።

ይህ ሰልፍ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ በመያያዝ ለሐገራችን እና ለወገናችን ደራሽ መሆናችንን፣ ድምፅ ለሌለው ወገን ድምፅ ለመሆንና ብሶቱን ለማሰማት አሜሪካና የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ትብብራቸውና ልገሳቸው ሕዝባችንን በቀጥታ በሚጠቅም እንጂ በተዘዋዋሪ መንገድ አፋኝ መንግስትን በሥልጣን ላይ ለማቆየት እንዳይሆን፡ እንዲሁም በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሚሰራቸው የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፡ ማሰርና መግደል፣ በዘር ማጥፋት ወንጀል (በአዲስ አበባ፣ በጋምቤላ፣ በአርባ ጉጉና በመሳሰሉት የተደረጉት የዘርና የሕዝብ ማጥፋት) ተጠያቂ እንዲሆን፣ በአንድነት ተነስተን ድምፃችንን ማሰማትና ለውጥ በሐገራችን እንዲመጣ ግፊት የምናደርግበት ጥሩና አመቺ አጋጣሚ ነው።

ይህንንም አመቺና ጥሩ አጋጣሚ ለመጠቀምና ለወገናችን ፍቅራችንን የምናሳይበት ሥራ ለመሥራት ታዲያ ምን ግብዣ ምን ቀስቃሽ ያስፈልገናል? ጋባዣችንም ቀስቃሻችንም ህሊናችን ነው። ማንም ጋባዥና ተጋባዥ ወይም አመስጋኝና ተመስጋኝ ሊሆን አይገባም። ሐገራችን ችግሯ ብዙ እንደመሆኑ ሁላችንም በቡድንም ሆነ በግለሰብ የተለያየ ችግሮቿን ይዘን ወጥተን በዚህ ሰልፍ ላይ በዝተንና ደምቀን ተገኝተን የዓለም ህብረተሰብ ችግራችንን እንዲረዳልን ለማድረግ ቆርጠን እንነሳ። ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ጓደኛ የምናውቀውንም የማናውቀውንም በመጋበዝ ሰልፉ የተዋጣለት እንዲሆን የበኩላችንን ከማድረግ አንቆጠብ፡ እንበርታ።

ሠላምና ፍቅር ከሁላችን ጋር ይሁን

ፍቅሩ ይበልጣል ነኝ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 2, 2009. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.