ህዝብ ለተቃውሞ እንዳይወጣ ወያኔ በየቀበሌው ህዝቡን ማስፈራራት ጀመረ

(EMF) በሰሜን አፍሪካ፣ እየተቀጣጠለ ያለው ህዝባዊ አመጽ አንባገነን በሪዎችን እየጠራረገ መምጣቱ ያሰጋው የመለስ ዜናዊ ስርአት በካድሬዎቹ አማካኝነት ህዝቡን በየቀበሌው እያሰባሰበ እና እያስፈራራ መሆኑን የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን አስታወቀ::

አንዳንድ ሃይሎች ብጥብጥ ለመፍጠር እየሞከሩ ነው በሚል ካለፈው እሁድ ጥር 22, 2003 ጀምሮ በየቀበሌ እየተጠራ ያለው ስብሰባ አላማ ወላጆችን “ልጆቻችሁ የአክራሪ ሃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ” የሚል ሲሆን ስለ ቱኒዢያ እና ግብጽ አብዮት ማውራትም ሆነ: ከሶስት በላይ አደባባይ ላይ በመሆን በጋራ መነጋገር ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑ ተነግሯል::

የኢትዮጵያ ህዝብ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሰፍኖ የቆየውን አምባገነናዊ ሥርዓት መንኮታኮት መጀመሩን በተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙሃን በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ዘጋቢያችን የገለጸ ሲሆን ሂደቱ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናትን በከፍተኛ ውጥረት ላይ እንዳስገባ አስታውቋል::

በተለይ በዩኒቨርሲቲና በኮሌጅ ግቢዎች አካባቢ በርካታ የደህንነት አባላት እየተሰማሩ መሆኑንም ታውቋል::

በሰሜን አፍሪካ እየተከሰተ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያውያንም እያነቃቃ እና እያነሳሳ ቢሆንም ህዝቡን ለለውጥ በአንድ ጊዜ ሊጠራ የሚችል የማህበራዊ ኔትወርክ ያለመኖሩ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል::

ህዝብን አፍኖ: የሃገሪቱን ሃብት እየዘረፉ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ ማስፈራራት የኢትዮጵያን ችግር አይቀርፈውም: ይልቁንም ሁኔታውን ያባብሰዋል: ሲሉ ባለፈው እሁድ ከተሰበሰቡት ወላጆች አንዳንዶቹ ተናግረዋል::

ብዙ ደም መፋሰስ ሳያስከትል በቱኒሲያ የተካሄደውን የመንግሥት ለውጥ፣ በግብፅ፣ ዮርዳኖስና ሱዳን እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ አመፅ አርአያነት በመከተል፤ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚታገሉ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥር 30 ቀን 2011 ባካሄዱት ዓለም አቀፍ ስብሰባ 20 አመት በኢጥዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ያለው የአቶ መለስ የአፈና አገዛዝ እንዲወገድ ጥሪ አቅርበዋል::

ይህንን ጥሪ ተክውትሎ  አንዳንድ የለውጥ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውም ታውቋል::

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 1, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.