ሃበሻ በየመን (ክፍል 3)

“ያሳዝናል” …ከማለት ጀምሮ የሰነዘራችሁት ብዙ..ብዙ አስተያየት ገነቢ ነው ተቀብያለሁ፡፡ ይገባኛል፡፡ በክፍል ሁለቱ ታሪክ ብዙዎቻችሁ ማዘናችሁ ደስ ብሎኛል፡፡ ሀዘኔን የሚጋራኝ በማግኘቴ እንጂ የሰው ስቃይ የሚያስደስተው ሳዲስት ሆኜ አይደለም ማዘናችሁ ደስ ያለኝ፡፡ እንዲያውም እኔ ላይ በደረሰው ሳይሆን ሰዎች ላይ የደረሰ ግፍ እና እልቂት በማየቴ በሀዘን፣ በጭንቀት.. በመንፈስ ጭንቀት ታምሜ የመን ያሉ ወገኖቼ አሳክመው አድነውኛል፡፡ ለዚህ ህዝቡ ምስክር ነው፡፡ በየቦታው የተሰነዘረው አስተያየት ይህ መፅሐፌን ተሳክቶልኝ ባሳትመው ምን ያህል መልዕክቱ ሊያስተምር፣ ሊያሳዝን፣ ወገን ለወገኑ እንዲያስብ ሊያደርግ..ይችልላል? የሚለውን እንዳስብ አድረጋችሁኛል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

   ይህ ‹‹…የወገኔን ስቃይ ለማየት የታደለው አይኔ እንባውን አንቆርዝዞ ማዳመጡን ለጆሮዬ ትቶታል። ልጁም ትረካውን ቀጠለ። በጣም አሳዛኝ የሆነ ነገርም በድጋሚ አየሁ። አይኔ ያቆረውን እንባ ገድቦ መያዝ አቃተው እና ለቀቀው። እናትህ ሞተች የተባልኩ ያህል አለቀስኩ፡፡ ሁለት ሆነው ለመታጠብ ከሚመጡት መካከል አንዱ ሁለት እግሩ የማይታዘዘው በሰው ታዝሎ የሚንቀሳቀስ ወገኔ ነው፡፡ ሁለተኛው አዛዩ ነው፡፡…………..

    ተጠጋኋቸው፡፡ እየተረከልኝ ያለውን ልጅ እጅ ይዤ ጎተት እያደረኩ ነው የተጠጋኋቸው፡፡ የእሱም እንዲያመልጠኝ አልፈልኩም፡፡

   ‹‹ሰላም ናችሁ?..እዚህች ጋር ልቀመጥ?›› ወረፋ ሊጠብቁ የተቀመጡበት ቦታ ተጠጋሁ፡፡

   ‹‹ወረ መጋላ ታኢ›› ተቀመጥኩ፡፡

   ‹‹እሺ..›› አልኩ ወጌን ለማሳመር ፈልጌ፡፡ ስለተደፈረው ወንድ ልጅ…ስሙኝማ በሞቴ ሰሞኑን ጁፔተር ሆቴል ተሰበሰቡ የተባሉት ጌዎች /ግብረሰዶማዊያን/ ህጋዊ ከሆኑ የሚደፈሩ ወንዶች ማየት እሲኪሰለቸን እኛም ሀገር ይገጥመናል ብዬ እፈራለሁ፡፡ ወደ ፊት ሴትኛ አዳሪ ብቻ ሳይሆን ወንድኛ አዳሪም ይኖረናል፡፡ ከአሁኑ አስበንበት ልንቃወም ይገባናል፡፡

   እዛው ሶማሊያ የገጠመኝ ታሪክ ውስጥ ልመለስ፡፡ ተራኪዬ በወንዶች የተደፈረውን ወንድ ልጅ እንዴት ወደ ቦሳሶ ይዘውት እንደመጡ እየነገረኝ ነው፡፡

   ‹‹ከጅጅጋ ፍየሎችና ድንች ጭኖ የመጣ ትንሽ..ትንሽ አማርኛ የሚችል ሹፌር አገኘንና የጠየቀንን ከፍለን ተጫንን፡፡ ምን ያደርጋል ቦሳሶ ከመድረሳችን በፊት መኪናውን አስቁመው ውረዱ ተባልን፡፡ ምንም አይነት ገንዘብ የለንም፡፡ ያለንን አሰባስበን ለባለመኪናው ሰጥተነዋል፡፡ ሲፈትሹን ምንም የለንም፡፡ ለምን ይፈልጉት ለምን ባናውቅም በዛ የበረሃ ሙቀት ከ9 ሰዓት የጀመርን ማታ ደረስ ጉድጓድ አስቆፈሩን፡፡በዚህን ጊዜ ልጁ መቀመጥም አይችልም፡፡ መቆምም አይችልም፡፡ ልብሳችንን ደልድለን አስተኛነው፡፡ በዛ ላይ እንዴት ለሽንት ይውጣ፡፡ ግራ እና ቀኝ ይዘነው ጮሆ..ጮሆ..ነው በመከራ….›› በሀሳቤ ሳልኩትና ሰቀጠጠኝ፡፡

   ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ ከፈለጋችሁ ሂዱ አሉን፡፡ የሚበላ ጠየቅናቸው፡፡ በልተው የተረፋቸውን ሰሀን ላይ ሳይከደን ተቀምጦ ነበርና ብሉ አሉን፡፡ ከነጋ ጠዋት ላይ ሻይ በዳቦ የበላን ነን፡፡ ተሻምተን በላነው፡፡ከቀማመስን በኋላ ያን የተደፈረ ልጅ እየተረዳዳን ደግፈን መንገድ ቀጠልን፡፡ስንንጓተት 250 ኪሎ ሜትሩን ሶስት ቀንና ሌሊት ፈጅቶብን ቦሳሶ ገባን፡፡….››ፖዝ አደረኩት እና ወደ አየሁት አዲስ እንግዳ ጫዎታ ጀመርኩ፡፡

  ‹‹እሺ… ሰላም ነህ?››

  ‹‹ፈያ..ፈያ..››አለኝ፡፡ ቅድምም በኦሮሚኛ ነው ያናገረኝ፡፡ አማርኛ የማያውቅ ከሆነ ለምን ሀገሩን ጥሎ እንደሚሄድና ምን መስራት እንደሚችል ለመጠየቅ ያሰብኩት አልተሳካም ማለት ነው? ብዬ ሰጋሁ፡፡

     ‹‹አማርኛ አትችልም?››

     ‹‹እችላለሁ ምን ፈለክ?››

      ‹‹ምንም እንዲሁ ለመጨዋወት ነው፡፡ አማርኛ ካልቻላክ አንግባባም ብዬ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ አንተስ?…››አልኩት፡፡

   ‹‹ናዝሬት ነኝ መናኸሪያ አካባቢ ነው መኖሪያዬም መስሪያዬም›› መስሪያዬም ሲለኝ ገረመኝ፡፡‹‹ምን ትሰራ ነበር?›› ስል የግርምቴን ጣራ ያንረው ወይ ያውርደው ብዬ ጠየኩት፡፡ አናረው እንጂ አላወረደውም፡፡

   ‹‹ልብስ ሰፊ ነበርኩ፡፡›› ግርምቴን ራሱ ገረመው፡፡ ሁለት እግሩም ከመታመሙ ጋር እንዴት እንደሚሰፋ ጠይቄው የሰጠኝ መልስ ይበልጥ አስደነቀኝ፡፡ በእግር የሚረገጠውን ብረት በሁለት ገመድ አስሮ… ቁጭት ተሰማኝ፡፡ ምነው በጋዜጠኝነት ስራዬ ላይ እያለሁ ባገኘሁት አልኩ፡፡ ስንት ሙሉ አካል እያላቸው ለልመና ቅርብ ለሆኑ ሰዎች ጥሩ ማስተማሪያ በሆነኝ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን አንድ ቀን ያስፈልገኛል ብዬ እየመዘገብኩ ባለው ማስታወሻ ደፍተሬ ላይ ስለምመዘግበው ብዙም ቅር አላለኝም፡፡

    ‹‹ለምን መጣህ? እዛው ሀገር ላይ መስራቱ አይሻልህም ነበር?›› አየኝ፡፡ አስተያየቱ የጤና አልነበረም፡፡ ‹‹ምን ትቀባጥራለህ? ማን ደልቶት ከሀገር ይወጣል?›› የሚል መልእክት ያለው መሰለኝ፡፡

    ‹‹እዚህ ለመስራት የሚያግደኝ ነገር አለ? የትም ቢሆን እሰራለሁ፡፡ግን ሀገር ላለመቆየት የወሰንኩት ብዙ ታግሼ ነው፡፡ አየህ ትውልዴ ወለጋ ነው፡፡ ምክንያቱ ሳይታወቅ ከሰባት ዓመት በፊት ማለት የ18 አመት ልጅ እያለሁ በአንድ ሌሊት እንዲህ ሆንኩ፡፡ በአደኩበት፣ በተማርኩበት ከተማ የሁሉ ከንፈር መምጠጥ ከቤት እንዳልወጣ አደረገኝ፡፡/አደራ አሁንም ከንፈር እንዳይመጡ/ የሚያውቀኝ በሙሉ ሲያየኝ ምን እንዲህ አረገህ? ከሚለው ጀምሮ የማይጠይቁኝ የለም፡፡ በመጨረሻም ያቺ የሰው ስሜት የምታኮላሽ ከንፈር መጠጣቸውን ይቸሩኛል፡፡ ልቤ ሲደማ ውሎ ያድራል…››

     ‹‹ከንፈር መጠጣ ሀዘኔታ አይደለም፡፡ ደም መጠጣ ነው›› ልቤ ልክ መሆኑን አሰመረበት፡፡ ንግግሩን ቀጥሎ ‹‹..መስራት እየቻልኩ ሠውን ሽሽት ቤት በመዋሌ ተጧሪ ሆንኩ፡፡ ከዛ መረረኝ፡፡ ጠፋሁ እና ሆለታ መጣሁ፡፡ ግን ማን ትሰራለህ ብሎ አምኖ ያሰራኝ? ሁሉም ሊረዱኝ እንጂ ሊያሰሩኝ አልደፈሩም፡፡ ከአመት በኋላ አማራጭ በማጣቴ  ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ አውቶቡስ ተራ ለትንሽ ጊዜ በልመና ተሰማራሁ እና የስፌት መኪና ገዝቼ መርካቶ ሸራ ተራ መስፋት ጀመርኩ፡፡ ለብዙ ጊዜ ሰራሁ፡፡ከሁለት አመት በኋላ ነገሮች ተበላሸብኝ ወደ ናዝሬት ሄድኩ፡፡..›› ይህን የመሰለ ጠንካራ ሰራተኛ ተስፋ ያስቆረጠው ነገር እንዳለ ገባኝ፡፡ በመስራት ማመኑን ከመጀመሪያው የወደድኩለት ባህሪው ነው፡፡

      ‹‹መርካቶ ጥሩ ትሰራ ከነበር ለምን ወደ ናዝሬት መሄዱ አስፈልገ? የተበላሸብህ ነገር…››አላስጨረሰኝም፡፡

  ‹‹የውልህ የተሻለ የራሴን ነገር /ሱቅ/ ለመክፈት አሰብኩና እቁብ ገባሁ፡፡ ሸራ ተራን ካወከው እዛ የታወቀ እቁብ አላቸው፡፡ መሀል ላይ አንድ ባለሱቅ ቁልፉን ሊሸጥ ሲል ልገዛው ተነጋገርን እና እቁቡን እንዲሰጡኝ ጠየኩ፡፡

     አላሳፈሩኝም፡፡

     ሰጡኝ፡፡ እንደዚህ ልጅ ያለ እያዘለ የሚያቀሳቅሰኝ ልጅ 12 ሺህ ብሩን ሰርቆኝ ጠፋ፡፡ እየሰራሁ መክፈሉን ተያያዝኩት፡፡ ብለው..ብለው አላልቅ አለኝ፡፡ ሰለቸኝ፡፡የተሰረኩትን ብር እንደሆን የምከፍለው ሳስብ ደግሞ ኑሮ ሁሉ ይመረኝ ጀመር፡፡ በዚህን ጊዜ ጥዬ ጠፋሁ፡፡ ናዝሬት እንደጠበኩት ባይሆንም ተቀጥሬ መስራ ጀመርኩ፡፡ የሚያስጠላኝ ነገር ግን መከሰቱ አልቀረም፡፡ሁሉም ከንፈር ይመጡና በሀዘኔታ እንደሚያሰሩኝ ይነግሩኛል፡፡ ተስፋዬ በመለምለም ፋንታ ጠወለገ፡፡ የተረጂነት ስሜት ከውስጤ አልወጣም አለ፡፡ ለምን ከንፈር ይመጡልኛል? ለምን የመስፋት ችሎታዬን አያደንቁም?.. ውስጤ ተጎዳ…›› ስጓዝ ውዬ ስጓዝ በማደሬ እንቅልፍ እያንጎላጀጀኝ ነው እዚህ ድረስ የሰማሁት…የሰማሁት፡፡

     ከዚህ ቦታ መራቅ እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡ የሚመጡትን ሁሉ እያየሁ ስሜቴ ተጎድቶ የራሴን መከራ ባልቻልኩበት ሰዓት ውስጤ በሀዘን እንዳይናወጥ ሰጋሁ፡፡ ለነገሩ ከዚህ በላይ..ከዚህ በከፋ ሁኔታ ውስጤ በሀዘን ይናወጥ ይሆን?

በሱማሊያዋ ቦሳሶ ከተማ ኢትዬጵያዊ እንደ ሰው ሲቆጠር አላየሁም፡፡ የወገኔን ስቃይ ወደድኩም ጠላሁም ከማየት ወደ ኋላ አላልኩም፡፡ አሁንም እያየሁ ነው፡፡ የጊዜ ሂደቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ እኔም የወገኔን መከራ ማየቴ እንዲሁ በግዴታ ቀጥሏል፡፡ ያማል..በጣም ያማል በሽታ ነው የሚሆነው፡፡ ዝርዝር የሱማሊያ መከራን መግለጽ ይከብዳል፡፡

   እኔ ጅብሪል እና አዲስ ያገኘነው ጣሂር አብረን ዋልን፡፡ ምሳ ፓስታ እና አሳ በእርጎ ተለውሶ በልተን 54.000 ሽልንግ ከፈልን፡፡ ከኬንያ የሚገባ ሜሮን የተባለ ጫት ጅብሪል ገዛ፡፡ ፍላጎት ስለሌለኝ አልገዛሁም፡፡ እህሉም የግዴን ነው የተበላልኝ፡፡ እሱ ሲቅም አብሬው ለመቀመጥ ሄድኩ፡፡ ብዙ የሀበሻ ምግብ ቤቶች መኖሩን ያኔ ነው ያየሁት፡፡ ውንክርክር ባለ የእንጨት ማገር ላይ በማዳበሪያ፣ በካርቶን እና በሳጠራ የተጋረደች ቤት ‹‹ኢትዮጵያ ሆቴል›› የሚል በእጅ የተፃፈ ፅሁፍ ተለጥፎባት አየሁ፡፡ በአይነ ህሊናዬ ሳጥን ቅርፅ እና ሽሯማ ከለር ያለው የአዲስ አበባው ኢትዮጵያ ሆቴልን ሳልኩት፡፡

  ‹‹እነሰናይት ጋር እንሂድ?›› የጅብሪል ጥያቄ ነው፡፡

  ‹‹ማናት ሰናይት እኔ እዚህ ከተማ ማንን አውቃለሁ አንተው በምታውቅበት ውሰደኝ››

   ‹‹እዛ ጨብሲም አለ››  

   ‹‹እኔ ምንም አልፈልግም ብቻ ሰዓቱን ማሳለፍ ነው የምፈልገው›› አልኩት፡፡ መንገድ ዳር የተሰራች ደሳሳ ሳጠራ የለበሰች ቤት ወሰደኝ፡፡ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ‹‹ውይ!..››የሚል ጩኸት ሰማሁ፡፡ ሁሉንም ሰላም ብለን ልንቀመጥ ስንል አንደኛዋ አንገቷን ሰብራ ራሷን ጉልበቷ ውስጥ ወሽቃለች፡፡ ሁሉን ካላወኩ እያለ ጥልቅ ጥልቅ የሚለው ስሜቴ ‹‹ለምን ይሆን? ምን ሆና ነው? የስደት ነገር…››እያለ ነገር ይበልታል፡፡

    ጅብሪል ‹‹ሰኒ ፍቅር ምን ሆንሽ?››አላት፡፡ ቀና አለች፡፡

    እኔም እንደ እርሷው መጮህ ነው የቀረኝ፡፡ በቆምኩበት ደርቄ ነው የቀረሁት፡፡ ለካ አይታኝ ነው የጮኸችው፡፡ አውቃታለሁ ታውቀኛለች፡፡ ሰናይት ቀይ የደስደስ ያላት ነች፡፡ አሳሳቋ ደስ ይላል፡፡ ከአፏ ብርሃን የምትተፋ ያስመስላታል፡፡ ተነስታ ጥምጥም አለችብኝ፡፡ እንባዋ ቁልቁል ተምዘግዝጎ ለመውረድ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ያደረኳት ስስ ሸሚዜን አልፎ ትከሻዬ ላይ ሞቅ ያለ ፈሳሽ ጠብ አለብኝ፡፡ ‹‹ምን አጋጣሚ እዚህ ጣላት? ሳዑዲ አረቢያ ናት ሲባል ሰምቼ አልነበር? እዚህ ተስማምቷት እየኖረች ነው ወይስ ለመሻገር ቀን እየጠበቀች?›› ጥያቄዎች ተገተለተሉብኝ፡፡

     ‹‹ግሩምዬ ምን እግር ጣለህ?››

     ‹‹አንቺን የጣለ እግር ነዋ!..››

‹‹አትቀልድ!!!..ስራህስ? ሚስትህስ? ልጅህስ?››ደረደረችው

     ‹‹ለመለስ ዜናዊ በአደራ ሰጥቼዋለሁ..››ብዬ ቀለድኩባትና ሌላ ሳትቀባጥር እቅፍ አድርጌ በጆሮዋ ‹‹ዝም በይ ስለ እሱ በኋላ እናወራለን›› አልኳት፡፡

    ‹‹ቧ!..ለልጅክ ጥለህ፣ ለሚስትህ ጥለክ ትመጻለህ?›› አለች ጓደኛዋ ጥፍጥ ባለ ኮልታፋ አማርኛ፡፡ ምላሽ የለኝም፡፡ ምንስ ማለት እችላለሁ?

    ‹‹አረ!…ምንድን ነው ነገሩ..እኔ ማመን አልቻልኩም፡፡ እኔ አላምንም፡፡›› በዚህም በዚህም ብላ ልታዋርደኝ ነው አለ ውስጤ፡፡ በዛ ላይ ሰርገው የገቡ የወያኔ ሰላዮች እንዳሉ ማንም እዛ ያለ ስደተኛ ያውቃል፡፡

     ‹‹እመኝ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡›› ቀልጄ ነገሩን ለማዘናገት ሞከርኩኝ፡፡ ሰነፍ ሰባኪ ቄስ ወይም ፓስተር የሆንኩ መሰለኝ፡፡ አጠገቤ ተቀመጠች፡፡ በዛ አረንጓዴ ነገር ለማየት አይን ፍለጋ በሚንከራተትበትና በማይሳካለት ምድረ በዳ ሳር ተጎዝጉዞ አረንጓዴ የናፈቀው አይኔን አጠገበው፡፡ ጭሱ እየተንቦለቦለ ከሰው ቁመት ስንዝር ከፍ ያለችውን ጣራ ተጋጭቶ እየተመለሰ ቤቷን አፍኗታል፡፡ ዳሷ ውስጥ ያሉት ጠቅላላ ይቅማሉ ሰናይትን ጨምሮ፡፡

    ሁለት ሀበሻዎች ጥግ ይዘው ካቲካላ ይጨልጣሉ፡፡ በእዚህች ዳስ ስር ይቃማል፣ ይጠጣል፣..ይዘሞታል፤ደስታ ውስጣቸው ሳይኖር ደስተኞች መስሎ ለመታየት መሞከር እርቲፊሻል ሳቅ፣ አርቲፊሻል ደስታ፣ ተሳቆ መኖር፣ ዳር ቆሞ ለሚመለከተው እንዴት ያስጠላል? ሰናይትን እዚህ ማግኘቴ ገርሞኛል፡፡ የጨርቆስ ልጅ ነች፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናት መሆኗን አውቃለሁ፡፡ አጠገብ ለአጠገብ ተቀምጠን ማውራት ቀጠልን፡፡ ‹‹ሳዑዲ አረቢያ መሆንሽን ነበር የማውቀው በምን ታዕምር እዚህ ተገኘሽ?›› እንደቀልድ ብጠይቃትም የማወቅ ጉጉቴ የነገር አንቴናውን ዘርግቷል፡፡

     ‹‹ሰናይት..ሰናይት..ቢዝነስ አገኘሁልሽ፡፡ያ ጣጤው ሱማሌ ዛሬ አብሮሽ ማደር ይፈልጋል፡›› እያለ አንድ ልጅ ገባ፡፡ ሴቶች አቃጥሮ በሚያገኘው ሳንቲም የሚኖር ወገኑን ሻጭ ነው፡፡ ደንግጨ ዞር ስል ሰናይት አፍራ በሻርፕዋ ፊቷን ሸፍናለች፡፡ መዝቀጧን በማወቄ… ጭኗን ከትዳር ፈታ ለገበያ ማቅረቧን በመስማቴ፣ በዙር በአዳር ተምና መሸቀጧ አሳፈራት….እንዴት ይሆን ደፍራ ቀና የምትለው? በጉጉት ጠበኳት፡፡

                    እቀጥላለሁ….ጠብቁኝ፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 7, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.