ሃሳብን በነፃነት መግለፅ አሸባሪነት ከሆነ… ገና ብዙ እናሸብራለን!!

በጋዜጠኝነት ሙያ ህዝብን ማገልገል፤ ወይም በፀሃፊነት ሃሳብን በነጻ መግለፅ “አሸባሪነት” ሊሆን አይችልም። ከዚህ መሰረታዊ እምነት በመነሳት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በሙያው ባለቤቶች ላይ፤ በአቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ውብሸት ታዬ እና ወ/ት ርዕዮት አለም እንዲሁም ተመሳሳይ ክስ በተመሰረተባቸው ኢትዮጵያዊያን ላይ፤ የኢህአዴግ አስተዳደር እያደረሰ ያለውን ግፍ እና በደል በፍፁም ልባችን የምናወግዘው ተግባር ነው። እየተፈጸመ ያለውን ድርጊትም በማውገዝ ብቻ በቸልታ አናልፈውም። የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ነጻነት እስከሚረጋገጥ ድረስ፤ የኢህአዴግን አስተዳደር በሁሉም የአለም መድረኮች ማጋለጣችንን እንቀጥላለን። Click here to read the full

አሸባሪነት ማለት ሰላማዊ ህዝብን ማፈንና መግደል ነው። አሸባሪነት ማለት በማን አለብኝነት ወይም በህግ ሽፋን፤ በህዝብ ላይ የጠመንጃ አፈ-ሙዝ ማዞር ነው። አሸባሪነት ማለት የህዝብን ሰላማዊ ኑሮ ማሸበር ነው። መንበረ ስልጣኑን በጠመንጃ የተቆጣጠረው ድርጅት በበርሃ ሽፍትነት፣ ብሎም በከተማ አሸባሪነት የቆየ የግድያ እና የአፈና ልምድ ያለው ሲሆን፤ የአሁኑ የእስር እና የአፈና ድርጊትም የከዚህ ቀደሙ የአሸባሪነት ተሞክሮ ውጤት ነው።

በአሜሪካ Homeland Security የሚረዳው Memorial Institute for the Prevention of Terrorism (MIPT) ህወሃትን ከአሸባሪ ድርጅቶች አንዱ አድርጎ ከፈረጀው አመታት ተቆጥረዋል። MIPT የአሸባሪ ድርጅቶችን የውስጥ ገመና እየበረበረ፤ የወንጀል ድርጊታቸውንም እየዘረዘረ በህዝብና በታሪክ ፊት ሲያጋልጥ የነበረ ሲሆን፤ የአሁኑ የወያኔ ድርጊትም የህወሃትን አሸባሪነት ማረጋገጫ፤ አባላቱንም በአለም ህዝብ ፊት መላገጫ እንዲሆኑ ያደረገትበትን አጋጣሚ ፈጥሯል።

ጠመንጃን ተገን አድርጎ በህዝብ ጫንቃ ላይ የተንሰራፋው ስርዓትና አራማጆቹ፤ የህዝቡን ሰላማዊ ኑሮ ለማተራመስ አማራጭ አድርገው የተጠቀሙበት መንገድ ጠንካራ ናቸው ያሏቸውን ተቃዋሚዎች፤ በአሸባሪነት ሰበብ ወደ ዘብጥያ መወርወር ሆኗል። “ሊበሉ ያሰቧትን አሞራ፣ ይሏታል ጅግራ” እንደሚባለው፤ ስርዓቱም ሊያስር የፈለገውን ወገን ያሻውን ስም እየሰጠ ማሰርና መግደሉ፤ ብሎም ዜጎች ለስደት እንዲዳረጉ በህዝቡ ዘንድ ከታወቀ ሰንብቷል። ይህ ባይሆንማ ኖሮ፤ ቦንብ እያፈነዱ ህዝብ የሚያሸብሩትን የራሱን አባላት ሸልሞ፤ ብልሹ የሆነውን ስርዓት በብዕራቸው ያንቀጠቀጡትን ጋዜጠኞች ማሰሩ የፈሪ በትር ከመሆን አያልፍም።

ይህ ብቻ አይደለም። “አሸባሪ” የሚለውን ስም በንፁሃን ዜጎች ላይ በመለጠፍ፤ በተሳሳተ የፖለቲካ ስሌት… የዲፕሎማቲክ ትርፍ ለማግኘት የታሰበው ጨዋታ፤ ገና ከጅምሩ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ግንዛቤን አግኝቶ፤ በምላሹ አሳሪዎቹ መሳቂያና መሳለቂያ ነው የሆኑት። በአጠቃላይ በአሸባሪነት ስም ለመግዛት የታቀደው ሸመታ፤ የስርዓቱን ብልሹነት አመላካች ከመሆን አልፎ፤ በኪሳራ የተጠናቀቀ፤ ስርዓቱም ወደ መውደቂያው ቁልቁለት እየተንደረደረ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ህወሃት/ኢህአዴግ ላለፈው የአሸባሪነት ተግባሩ፤ ህዝብን ይቅርታ በመጠየቂያ ጊዜው፤ ኢትዮጵያዊነትን እያፈራረሰ እና የህዝብን ሰላማዊ ኑሮ እያተራመሰ ይገኛል። የህዝቡን ማህበራዊ ኑሮ እመቀመቅ እየጨመረ፤ ንፁሃን ዜጎችን እያሰረና እየገደለ… ህዝቡ በጨለማ እንዲዳክር በማድረግ የጥቁር ሽብር ተልዕኮውን ቀጥሎበታል። ከዚያ አልፎ ግን የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ለህዝብ ከመቆም ውጪ የአሸባሪነት ድርጊት ፈፅመው አያውቁም፤ አልፈጸሙም ወይም አላስፈጸሙም።

ይህ ጊዜ ያልፋል። አገርና ህዝብ ግን አያልፍም። የሁሉም ተግባርና ድርጊትም በታሪክ ሚዛን ላይ ተቀምጦ ህዝብ ፍርዱን ይሰጣል። በዚያን ጊዜ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ የታሪክ ምዕራፍ በአሸባሪነቱና በአረመኔነት ሲጠቀስ፤ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ የራሳቸውን ጊዜና ህይወት ሰውተው ለትውልድ ላበረከቱት መልካም ተግባር ይወደሳሉ። በእሳት የተፈተኑት እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆችም የብዕር ጦራቸውን፤ የሃቅ በትራቸውን በአረመኔዎች ይሰነዝራሉ። ሃቅ መጻፍ አሸባሪነት ከሆነ፤ እንደትላንቱ ሁሉ…. ዛሬም ሆነ ወደፊት በብዕራችን አዳፍኔ ሊያሸብሯችሁ ሙሉ አቅም ያላቸው ጋዜጠኞች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር አሉ። በ’ርግጥ ሃሳብን በነፃነት መግለጽ አሸባሪነት ከሆነ… “አሸባሪዎች” የተባሉትን ጋዜጠኞች ብዕር አንስተን፤ ጥቁር ሽብር ያፋፋሙትን የኢህአዴግ ተቋማት፤ በሽብር ማንቀጥቀጣችን በእርግጠኝነት የሚቀጥል ይሆናል።
[የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ) እና በስደት ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች በጋራ]

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 24, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.