ሁለተኛው ቀን እንዲህ አለፈ!

EMF – (ዳዊት ከበደ ወየሳ እንደዘገበው) ሁለተኛው ቀን። በተለምዶ 2ኛ እና 3ኛው ቀን ግርግር እና ትርምስ የማይበዛበት፤ ረጋ ያለ ሁኔታ የሚታይበት እለት ነው። እኛም በጠዋት መሄዳችንን ትተን አመሻሽ ላይ ወደ ሜሪላንድ ስቴዲየም ለመሄድ አሰብን። ጓደኛዬ ክንፉ አሰፋ ዲሲ ዱካም ሬስቶራንት፤ እኔ ደግሞ ስካይ ላይን የሃበሾች ሰፈር ቆይታ አድርገን ነበር። ስካይ ላይን ለመኪና ማቆሚያ ቦታ የለም። እያንዳንዱ ምግብ ቤት እና የሃበሻ ሱቅ ጢም ብሎ ሞልቷል። ዲሲም እንደዛው ነው አሉ። ህዝቡ ደግሞ ከሃሙስ በኋላ በብዛት ወደዚህች ከተማ ይጎርፋል፤ ያንጊዜ ከዚህ የባሰ ግርግር እንጠብቃለን። በሌላ በኩል የዲሲው ዱከም ሞቅ ደመቅ ብሏል። በሰፊው ወሬ ከያዙት መሃል ብዙዎቹ ስለፌዴሬሽኑ ጉዳይ ያወራሉ። የወሬያቸው መነሻም፤ ትላንት እኛ የጻፍነው ዘገባ ነው። ከዚያ በመነሳት የአንዱን ድምቀት እና የሌላውን ውድቀት እያወሩ መቆየታቸውን ነው፤ ጋዜጠኛ ክንፉ የነገረኝ።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ለኛ ሁለቱም የኢትዮጵያውያን ድርጅት ነው። ባይከፋፈሉ ደስ ይለናል። እነ አያያ፣ ሰብስቤ፣ እንዳለ ቱፋር፣ ዮሴፍ፣ ብስራት እና ሌሎችም የፌዴሬሽኑ መስራች አባቶች ናቸው። በፌዴሬሽኑ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በወርቅ ቀለም ሊጻፍ ሲገባው፤ ከስፖርት ቲማቸው እና ከፌዴሬሽኑ ወጥተው የራሳቸውን ማህበር ማቋቋማቸው፤ የኩርፊያ እና የእልሃቸውን መጠን ያሳያል። ዲሲ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጁት ድግስ ላይ ሼኽ መሃመድ አላሙዲን አለመገኘታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውም ተሰምቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚቀጥለውን 31ኛ አመት ዝግጅት ከነባሩ ፌዴሬሽን ጋር ለማክበር መፈለጋቸውንና አብረው የሚያከብሩ ከሆነም ገንዘብ እንደሚፈቀድ ሲወራ ተሰምቷል። “እውነት ይሆን?” በዘገባችን መጨረሻ ላይ ምላሽ እንሰጥበታለን።

እናም ሜሪላንድ ወደሚገኘው ፌዴሬሽናችን አቀናን። እንደትላንቱ ከፍለን ልንገባ አሰብንና ሃሳባችንን ቀይረን ጋዜጠኞች በሚገቡበት በር በኩል ሄድን። የሚተባበረን አጥተን ጥቂት ደቂቃዎች እንደቆየን፤ የፌዴሬሽኑ ምክትል፤ ቴዲ መጥቶ ይቅርታ ብሎ አስገባን። መታወቂያ ያላገኙ ስፖርተኞች እና ነጋዴዎች ጭምር እንደትላንቱ ተሰልፈዋል። የቀድሞው የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዘዳንት አብዩ መታወቂያ እያተመ ይሰጣል። እኛ የጋዜጠኛነት መታወቂያችንን ብናገኝም፤ በዚህ በመታወቂያ ጉዳይ የሚጉላላው ሰው ብዙ ነው። በዚህ ጉዳይ ፌዴሬሽኑ አንድ መላ ማበጀት ይኖርበታል። ሁልጊዜ ነጻ መታወቂያ በነጻ እያደለ መቀጠል አይኖርበትም። ኳስ ተጫዋቾቹን ጨምሮ ሌሎች ባለጉዳዮች ተመጣጣኝ ክፍያ በማድረግ፤ አገልግሎት ሰጪውም፤ ለስራው ተመጣጣኝ ክፍያ እያገኘ ስራው መሰራት አለበት። የራሳችንን ጉዳይ ስናወራ ዋናውን ዘገባ ዘነጋነው።

ወደ ውስጥ እንደዘለቅን የጥብስ እና የአበሻ ምግብ ሽታ አወደን። ከዚያው ጋር ተከትሎ ታዲያ ምሬት አዘል ቅሬታ ከነጋዴዎች በኩል መስማታችን አልቀረም። የኤሌክትሪክ ሃይል በተደጋጋሚ እየጠፋ ስራ ለመስራት ተቸግረዋል። በተለይ የኤሌክትሪክ ምድጃ ያመጡ ሰዎች አምርረው ሲማረሩ ነው የሰማነው። ተጨማሪ ጄነሬተር ተደርጎ ይህ ችግር ካልተቀረፈ፤ በቀጣዩ ቀናት ነጋዴዎቹ የተቃውሞ ሰልፍ የሚያደርጉ ነው የሚመስለው። እንደዚያም ሆኖ ግን እየሰሩ ናቸው። ባለን የቆየ ልምድ መሰረት፤ ከሃሙስ ጀምሮ ደግሞ ተዘጋጅቶ የመጣ ነጋዴ፤ በያንዳንዱ ቀን ቢያንስ 3ሺ ዶላር እና ከዚያ በላይ ይሰራሉ። ምናልባት እንዲህ የበዛ ገንዘብ መቁጠር ሲጀምሩ የሆነውን ነገር ሁሉ ይረሱት ይሆናል። ችግሩ ከቀጠለ ግን ለፌዴሬሽኑ የራስ ምታት ነው የሚሆኑት – እናም በድጋሚ “ይታሰብበት” ብለን ይህን በዚህ እንለፈው።

ለነገሩ እግር የመራን ወደ ሜሪላንዱ ስቴዲየም ይሁን እንጂ፤ የዲሲውም ዝግጅት መከናወኑ አልቀረም። እዚያ ሄዶ የነበረ አንድ ጋዜጠኛ ግን አጋጥሞናል። “እንዴት ነው ማዶ ሰፈር?” አልነው። ምንም መናገር የፈለገ አይመስልም። ጭንቅላቱን እየነቀነቀ የሃዘን ምልክት ሰጠን። በአፉም ተናገረ ወይም በምልክት ነገረን ትርጉሙ አንድ ነው። እኛም የምንሰማውን ብቻ ከጻፍን ጥሩ ስለማይመጣ በአንዱ ቀን እዚያ መሄዳችን አይቀርም፤ ብለን ነገሩን በይደር አሳልፈነዋል። ለጊዜው ግን ባለመሄዳችን በኛ በኩል ምንም የምንለው ነገር የለም።

ወደ ሜሪላንድ ልንመልሳቹህ ነው። የመጨረሻው ጨዋታ በዲሲ እና በቶሮንቶ መካከል የተከናወነ ነው። ተመልካቹ ጨዋታውን የሚመለከት አይመስልም። ግን አሪፍ የተሳተች ጎል ሲያይ መጮሁ አልቀረም። መቼም መሳት ብቻ ሳይሆን እራሳችን ላይ ማግባትም እየቻልንበት ይመስላል። ከዲሲ እና ቶሮንቶ ጨዋታ በፊት… የነማን ቡድን እንደሆነ ባላውቅም፤ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ሴኮንዶች ሲቀሩ ለራሱ በረኛ ያቀበለው ኳስ፤ በረኛውን ሸውዳ ጎል ገብታለች። በራሱ ላይ ጎል አስቆጥሮ… ጨዋታው እንደተጀመረ፤ የመሰናበቻ ፊሽካ ተነፍቶ ጨዋታው ተጠናቀቀ። አንድ ነገር ልብ ብላቹህ ይሆናል – ሜዳው ውስጥ ማን እና ማን እንደሚጫወት ብቻ ሳይሆን ስንት ለስንት እንደወጡም አይታወቅም። ስቴዲየሙ ነጥብ ማሳያ ቦርድ አለው። ፌዴሬሽኑ ግን ከዚህ በፊትም ሆነ አሁን ይህንን የነጥብ ማሳወቂያ ቦርድ ሲጠቀም አናይም። ምናልባት “ኢትዮጵያውያን ነጥብ ማወቅ አያስፈልጋቸውም!” ካልተባለ በስተቀር፤ ቦርዱን በጥቅም ላይ ማዋል አስፈላጊ ነው። ይህ ባለመሆኑ በተደጋጋሚ ገባ ወጣ እያሉ ጨዋታውን ለሚከታተሉ ሁሉ ሁኔታው አሰልቺ እና ደባሪ ይሆንባቸዋል። ስንት ለስንት እንደሆኑ ለማወቅ ዘጠና ደቂቃውን ሙሉ እዚያ መቀመጥ ያስፈልጋል። ስቴዲየሙ ውስጥ ተቀምጠውም ቢሆን እንኳን እነ አቶ ዘውገ ቃኘው ነጥቡን፤ በድምጽ ማጉያ ካላሳወቁ በቀር፤ ተጫዋቾቹ በሜዳ ውስጥ እንቡር እንቡር እያሉ ሲንፈራገጡ እና ተመልካቾችም ሜዳው ላይ ሲያፈጡ ብቻ ነው የምናየው። እናም የነጥብ ማሳወቂያው ቦርድ ነገር “እባካቹህ ይታሰብበት” እንላለን። እኛም ዲሲ እና ቶሮንቶ ስንት ለስንት እንደወጡ ብቻ ሳይሆን፤ የትኛው ለየትኛው እንደሚጫወት ሳናውቅ ስቴዲየሙን ለቀን ወጥተናል።

ከወጣን በኋላ የምንሄድበትን አቅጣጫ ለማስተካከል GPSአችንን ማናገር ስንጀምር የፌዴሬሽኑን ፕሬዘዳንት ጌታቸው እና የቀድሞውን ህዝብ ግንኙነት ፋሲልን አይተን የመኪና ጥሩንባ ነፋንላቸው። የሞቀ ሰላምታ ተከተለ። ከሰላምታችን በኋላ የህዝቡን ስሞታ አቤት አልን። ከስሞታው በኋላ የሰሞኑን ሃሜታ ሹክ አልናቸው።

“እዚያ የተሰጠው ገንዘብ፤ ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ወደናንተ እንዲዞር ተብሏል። እውነት ነው?” ብለን ጠየቅናቸው። ሁለቱም በመገረም ተያይተው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነገሩን።
“ወደፊት አብራቹህ የመስራታችሁስ ነገር?”
“እነሱ እኮ ናቸው ፌዴሬሽኑን ጥለው የሄዱት።”
“እና ወደፊት አብራቹህ ትሰራላቹህ?”
“አሁንም ሆነ ወደፊት እነሱ ያሉበት የስፖርት ቲም ከመለሳቸው እና ከወከላቸው ወደ ፌዴሬሽኑ የማይመለሱበት ምክንያት አይታየንም።”
ተባብለን ሌላም ሌላም አውርተን፤ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ብሂል ተለያየን። የኛው የትላንት ውሎ ዘገባችን እዚህ ላይ ያበቃል። ዛሬ ከሰአት በኋላ የቀድሞ ጋዜጠኞች ትንሽ የምሳ ግብዣ ቢጤ ስላለችብን ወደ ስቴዲየሙ የምንሄደው ረፈድ አድርገን ነው። ቢሆንም ከመሄድ አንቀርም እና ዘገባችን ይቀጥላል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 2, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.