ሀበሻ በየመን (ክፍል 8)

(በግሩም ተክለሃይማኖት)

እዚህ የሰው ልጅ መሰቃያ ቦታ /አልቀረስ ካምፕ ውስጥ/ ስደተኛውም በዘር፣ በጎሳ፣ በእምነት፣ ተቧድኖ የሚባላበት ቦታ ለምን አልገባህም ተብዬ ዱረብል ሶሊሽን አታገኝም የተባልኩት ለምን ይሆን? ሞቴ የሚፈለግበት ምክንያት ይኖር ይሆን? ኤጭ ድከም ብሎኝ ነው እንዲህ ይህን ማሰቤ…እንግዲህ እኔም እንደ የመኑ ፕሬዘዳንት አሊ አብደላ ሳላህ 32 አመት የመንን ሙጥኝ ልል ነው ወይስ እንደ እሳቸው ለየመን ህዝብ ሰሰለቸው በሰላማዊ ሰልፍ ‹‹ይርሀል›› ይሂድልን ልባል ነው? ወይ ጉዴ!!! ወይ ወገን ማጣት……ብዬ ነው ክፍል ሰባት ላይ የተሰነባበትነው፡፡

..አል-ቀረዝ የተባለው ካምፕ ውስጥ እየተሰቃዩ ያሉትን ወገኖቼን ሁኔታ ለማየት ጉዞዬን ወደዛ ያደረኩት ባለፍው ሳምንት ነበር፡፡ ያየሁትን ሁሉ እንደምናወጋ ቃል ገብቼ ዛሬ በየመኒዎቹ ዘንድ ‹‹ዱኒያ ዮም አሰል ዮም በሰል›› የሚሉትን አባባል ልጠቀምበት ፈለኩ፡፡ ህይወት አንድ ቀን ማር አንድ ቀን ሽንኩርት ናት እንደማለት ነው፡፡ አንድ ቀን ማር ሆና ስታስቅ አንድ ቀን ሽንኩርት ሆና ታስለቅሳለች ማለታቸው ልክ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ.. ዛሬ ሁሌ ስለምናነሳው መጥፎ ስቃይ በይደር እንተወውና ዘና ያለ ዘና የሚያደርግ እናውራ፡-

የመን እንደመጣሁ 40 ጂኒ ሲባል እሰማለሁ፡፡ ጂኒ ማለት ሴጣን መሆኑን ቀድሜም አውቃለሁ፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው 40 ሴጣን ያሉት? የሰራው ሲወራ በጣምም ይጋነንለታል፡፡ የተንኮሎች አባት የሴጣኖች ደቀ-መዝሙር ተደርጎ ይወራል፡፡ ልክ እንደአለቃ ገብረሃና ቀልዶች ሁሉ ተሰብስበው ለሱ ተሰጥተዋል፡፡ ያን ስል ግን እሱ ያልሰራውም ተደምሮለታል ለማለት ነው፡፡

ተንኮል ካለ እሱ የተባለ ይመስላል፡፡ ሰዎች ራሳቸው የሰሩትን የእሱ አድርገው ያወሩለታል፡፡ እሱ ግን ምን ቢጥም የእሱ ካልሆነ አይቀበልም፡፡ ይህን ሰው ለማግኘት ካሰብኩ ዋል አደር አልኩ፡፡ ስለ እሱ የሰማሁት እውነት የማይመስሉ ነገሮችን ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ እንደተመኘኋት አገኘኋት.. የሚለውን ያስቀነቀነኝ ቀን ከቀናቶች ገጥሞ አገኘሁት፡፡ ሰው ባይሰማውም ‹‹ያሰብኩት ተሳካ..ያለምኩት ደረሰ..››የሚለውን በውስጤ ያቀነቀንኩበት ቀን ገጠመኝ፡፡ አራት ኪሎ ሆቴል የሚባል ቦታ በጠዋት ቁርስ ለመብላት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አንድ ጠረጴዛ ላይ ተሰይመናል፡፡ ጠቆር ያለ ረጅም፣ ቁመናው ደስ የሚል ሰው፣ ፈገግታው የለበጣ ይመስላል በነፃ ቸሮን ገባ፡፡ ገና ጠዋት ቢሆንም ጫቱ አፉን ሞልቶታል፡፡ የሚያመነዥግ በግ እንጂ በጠዋቱ እየቃመ አልመሰለኝም፡፡ ሐረሮች ኢጃባና እንደሚሉት መሆኑ ነው፡፡ ሀገር ቤት እያለሁ ወደ ጅማ አንድ ገጠር ውስጥ ‹‹ሁዱ በና›› ብለው በጠዋት ሲቅሙ አጋጥሞኛል፡፡ ኦሮምኛ የማትችሉ ፍችውን ጠይቁ..እኔ አልናገረውም፡፡

‹‹..መስከረም ቁርስ ምን አለ?..›› እንዴት አባቱ ድምፁ ያምራል! አልኩ በውስጤ መስከረም የምትባለው ምግብ ሰራተኛ ፍርፍር መኖሩን አበሰረችው፡፡ ‹‹ሂሽ!…እንጀራ በእንጀራ አልፈልግም፡፡ እንጀራ ትላለች እንዴ አታፍሪም? እኔ እሱን ሽሽት ፓስፖርት አውጥቼ ቪዛ ብዬ በኤርፖርት ስገባ እሱ ፓስፖርት አላለ፣ ቪዛ ቀድሞኝ እዚህ ነው ያገኘሁት ሲያስጠላ!!…›› ትንሽ ፈገግ አስባለኝ እንጂ ብዙም አላሳቀኝም፡፡ እንጀራን በመናገሩ ቂም ይዤበት ይሆን? ሌላ ጆሮዬን የቆፈረ ድምፅ ትኩረቴን ሳበው፡፡

‹‹አይ አርባጂኒ…›› አለች በቀልድ፡፡ ለእኔ ግን የምስራች እንማለት ነው የሆነልኝ፡፡ ይሄ ነው ማለት ነው 40 ጂኒ አቤት ደስታዬ….!!!! እውነትም ሴጣን ይመስላል፡፡ ግን ሴጣን ጥቁር ነው ያለው ማነው? ነጮቹ.. የእኛ መልዓኮች ናቸው ሴጣንን አፍሪካዊ ያደረጉት አይደል? ይህ ሀሳብ ከውስጤ ለሁል ጊዜውም እንዲወጣ ተመኘሁ-ጥቁርን ከሴጣን ጋር ማመሳሰሉን ማለቴ ነው፡፡ ‹‹አርባ ጂኒ አንተ ነህ?›› ንጣትን ጥሎ ቀላትን ባስተናገደ አይኑ አተኮረብኝ፡፡ ፈገግ ሲል ጥርሱ ላይ የተለጎደው ጫት ታየኝ፡፡ መጣና አጠገቤ ወንበር ስቦ እየተቀመጠ ‹‹አዎ ምነው? ፈለከኝ›› አለ፡፡ ለከተማው አዲስ መሆኔን ሳያውቅ አልቀረም፡፡

‹‹እንደሰማሁት ብዙ ጊዜ በባህር ነው የተመላለስከው ይባላል፡፡ ታዲያ የትኛውን ፓስፖርት ነው ያልከው ወይስ ስላንተ የሰማሁት በባህር..ጅቡቲ..ሱዳናዊ ነኝ ብሎ..የሚባሉት ነገሮች ውሸት ናቸው?›› ወደቀልድ ወስጄ ነው አጠያየቄ፡፡ እሱ ምንም ሳይመስለው እውነት መሆኑን ነገረኝ፡፡ ጥያቄዎቼን አዘነብኩለት..ለካ ሳላስበው ጥያቄ እያከታተልኩ ወጥሬዋለሁ፡፡ ምነው አጣደፍከኝ ብሎ ተነስቶ እስከሄደበት ሰዓት ድረስ አወራን፡፡ ያወጋኝን እኔስ ምን መቋጠሪያ ኖሮኝ እሸሽገዋለሁ…ልዘርግፈው!!

ስለአንተ ስሰማ የአለማችን የመጀመሪያው አውሮፕላን ላይ ለማኝ ተብለህ ዱባይ የሚታተም መጸሔት ላይ ወጥተሀል ይባላል እውነታውን ንገረኝ እስኪ…ሀገራችን በልመና  ብትታወቅም አንተም አስጠርተሃታል ጎበዝ!!!….ቀልደኛ ቢጤ ስለሆነ በቀልድ አጀብሉለት፡፡

‹‹እውነታው እውነት ነው፡፡ ይህን ያደረኩት እኮ አውቄ አይደለም፡፡ በመሰረቱ እኔ የደርግ ሰራዊት ነኝ፡፡ ያሲን ነው ሰሜ፡፡ በዚህ ግን ማንም አያውቀኝም፡፡ እኔም ይህን ስም ረስቼዋለሁ፡፡ ሲጠሩኝ ዞር አልልም፡፡ ህፃን አዋቂው 40 ጂኒ ይለኛል፡፡ እኔም ተስማምቶኛል፡፡ ይህን ስያሜ አሰጥቶ ስሜን ያስረሳኝን ስራ ከጀመርኩት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ላውጋህ፡፡ የሐረር ልጅ ነኝ፡፡ ሰራዊቱ ውስጥ እያለሁ ኤርትራ ነበርኩ፡፡ ያኔ ከኤርትራ ስንመለስ አዲስ አበባ ላይ ስንራብ ስንለምን ስንት ስንት አሉን፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ‹‹ለምን ጠንክራችሁ አትዋጉም ነበር? ወደ ቤተሰብ አትመለሱም..››የመሳሰሉት አባባሎች ውስጤ መጥፎ ስሜት ጭረውብኛል፡፡

ወደቤተሰብ ጋር ብገባስ ምንድነው የሚጠብቀኝ አልኩና ጅጅጋ ላይ ጀለቢያየን አድርጌ ኢማማዬን ጠምጥሜ ‹‹ከሱዳን የመጡ አዋቂ ሼህ..›› ብዬ አስወራሁ፡፡ ጥቁረቴና ርዝመቴ ረድቶኛል፡፡ /በትክክልም ሳስተውለው ሱዳናዊ ይመስላል/ ሰዉ ለማስጠንቆል ተዥጎደጎደ፡፡ ልክ ዛር እንዳለበት እገዝፍ ሁሉ ነበር፡፡ ሁለት አብሪ /መረጃ የሚሰጡኝ ልጆች ሰዉ መሀል አስቀምጣለሁ/ ትንሽ ሸቀልኩና ወደ ጅቡቲ ነካሁት፡፡ እዛም ዝናየን በሰፊው አስወራሁና በጥንቆላው ተሰማራሁ፡፡ ሁለት ሚስቶችም አገባሁ፡፡ ስኬታማ ሆንኩ በማጭበርበሩ..፡፡ ብዙ ተጠቀምኩ፡፡

እንዴት ግን ሊሳካልህ ቻለ? የሚል መጠይቄን ሰማና አየኝ፡፡

‹‹ዋናው ሳይኮሎጂ መጠቀም ነው..ሰዉ በችግር ስለተተበተበ የምትለው ሁሉ መፍትሄ መስሎ ይታየዋል፡፡ ለምሳሌ እዚሁ ሰነዓ ውስጥ የገጠመኝን ልንገርህ፡፡ የሆኑ ልጆች ጋር ና አሉኝ እና ልቅም ጫቴን ይዤ ሄድኩ፡፡ እዛው ቁጭ ብዬ ቡና የምታፈላው ልጅ ከሶስቱ ሴቶች ጋር በትንሹም በትልቁም ትላከፋለች፡፡ አየኋትና አንቺ ሴት ልጅ እጣ ፋንሽ አይደለችም አልኳት፡፡ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች እና ልክ ነህ አንተ ገና እውነታውን አየህልኝ  አወክልኝ አለች፡፡ አስብ ያለነው ሁለት ወንዶች ነን ከኛ አልተጣላችም፡፡ ከሴቶቹ ተጣላች ምን ማስረጃ ያሰፈልገዋል ያየሁትን ነገርኳት፡፡ ሁሉም ስራዬ እንዲሁ ነው፡፡›› ይህች ሴት እጣ ፋንታሽ አይደለም ብሎ ያሰለቀሳት ልጅ ዛሬ አንድ ፎቅ አብራኝ ያለች ጎረቤቴ ሆናለች፡፡ የአውሮፕላኑን ታሪክ እንዲያወራኝ ፈለኩ…

‹‹ እሺ ወደ አውሮፕላኑ ታሪክ ስመልስህ…ከየመን ወደ ዱባይ በኦማን በኩል አቋርጠን ሄድን፡፡ እድሌ አልሆነም እና ተያዝኩ፡፡ ከእስር በኋላ ወደ ሀገሬ ስመለስ ትዝ አለኝ፡፡ ምንም የለኝም፡፡ ከኤርፖርት እንደወጣሁ ለታክሲ የሚሆን..ሌላው ቀርቶ  ወደ ሐረር የምሄድበት እንኳን የለኝም፡፡ ያ- ጠንክረህ አትዋጋም ነበር? ያለኝን ሕዝብ ፊት ዳግም በልመና አይኑን ላይ… አልኩና አፈፍ ብዬ ተነሳሁ፡፡አውሮፕላን ውስጥ ጃኬቴን አወለኩና ልመናዬን ጀመርኩ፡፡ በአረቢኛ፣ በእንግሊዘኛ እና በአማርኛ ነው ልመናዬን ያጧጧፍኩት፡፡ አንዱ ካሜራ አወጣ እና ፎቶ አነሳኝ፡፡ ምንም ያርግ ብቻ ገንዘብ ይሰጠኝ፡፡ አፋጥጨ ተቀበልኩት፡፡ ፎቶዬ ያለበትን መፀሔት ከዱባይ በሶስተኛው ወር ላኩልኝ፡፡

ልላ ገጠመኝ እንዲያወራልኝ የጠየኩት አንድ ለቅሶ ላይ ተገናኝተን ነበር፡፡ ሰዉ ሁሉ የሚያውቀው ገጠመኙ ነው፡፡ ግማሽ ጎኗ የመናዊ የሆነች ሴት ከሱዳን የመጣ ሼህ ነው ተብሎ ቤቷ ትጋብዘዋለች፡፡ ሀእ!..ህእ!…ሀሀሀ!!!..እያልኩ ማክላላት ጀመርኩ፡፡ በዛ ሰዓት የጫት አራራ ጠሮብኛል፡፡ ‹‹አቤት!…አቤት!.. ተቆጣ..›› ስትል ደስ አለኝ፡፡ አጓራሁ..አጓራሁ እና የታል ጫቱ የታል በጉ እልኩና በሰፊው አጓራሁ፡፡ ‹‹የዛሬን ተለመነኝ..የዛሬን!!..›› እያለች ጫቱ ተገዛ በጉም መጣና ታረደ፡፡ ስንበላ፣ ስንቅም፣ ስጠነቁል ታደረ፡፡ ወደ ሁለት መቶ ዶላር ተሰጠኝ፡፡ በሌላ ጊዜ ኮሚኒቲ ውስጥ ካርታ ስጫወት ባሏን ፈልጋ ይሁን ለሌላ ነገር ረሳሁት ስትመጣ አየችኝ፡፡ ‹‹እ!..›› ድንጋጤዋን ተወው፡፡ ወዲያው ወገቧን እንደ ዳንኪረኛ ይዛ ‹‹ እነሼህ ሙልጭ!!!… እነሼህ ቁልጭ…አፈር ብላና አንተ አጭበርባሪ..›› አለችና ጫማዋን አውልቃ ልትደበድበኝ ነበር፡፡

ልጆቹ ሳይሰልሙ ሰለሙ ብለህ… እውነት ነው? የሰማሁት እውነት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ሰለሙ ከተባሉት ልጆች አንዱ ቀድሞውኑ ሙስሊም የነበረ ልጅ ነው የነገረኝ…ከሱ አንደበት ስሰማው..

ሁኔታው የተፈፀመው አደን ነው፡፡ ወደ ሰነዓ መምጣት ፈልጌያለሁ፡፡ ከሰነዓ በኋላ ወደ ሳዑዲ ለመሄድ ነው እቅዴ…:: ያለኝ ሳንቲም ትንሽ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ በባህር የመጡ ልጆች አገኘሁ፡፡ ምንም ልሰጣቸው አልቻልኩም፡፡ ለእነሱም ሳንቲም ማግኛ ዘዴ ፈለኩ፡፡ ለሁሉም ብለኝ ሳንቲም ጀለቢያ እና ኢማማ ገዛሁላቸው እና በማግስቱ መስጊድ ወሰድኳቸው፡፡ ‹‹እነዚህን ክርስቲያኖች ስለቁራን ነግሬ እምነታቸውን ሊለውጡ ይፈልጋሉ፡፡ የምችለውን ያህል አስተምሬያቸዋለሁ የበለጠ ተምረው እዚሁ እስልምናን እንዲቀበሉ ይፈልጋሉ፡፡›› አልኩና በስግደት ሰዓት ተናገርኩ፡፡ እስከዛው እየበሉ እዚሁ እንዲከርሙ እርዷቸው ብዬ ጨርቅ አነጠፍኩ፡፡ 100 ሺህ አካባቢ /500 ዶላር/ ተሰበሰበልን፡፡ ያቺን ያዝኩና ከልጆቹ ጋር ወደ ሰነዓ ሄድን እዛም እንዲሁ አደረኩ እና ለእነሱ ሳንቲማቸውን አካፍያቸው ወደ ሳዑዲ ሄድኩ፡፡

ጠዋት ሁለት ሰዓት ላይ ጫት ጉንጩን ሞልቶት ነው የሚታየው፡፡ አንድ ሰሞን አፈሳ ነበር፡፡ ሳያስበው ጠዋት ሊይዙት ደረሱ፡፡ ያኘከውን ጫት ከአፉ አውጥቶ..ፊቱን፣ጉንጩን ሁሉ ቀባና ግንቡን ተጠግቶ ስልክ እንደሚያወራ ‹‹ሀሎ!›› እያለ ጮክ ብሎ ማውራት ጀመረ፡፡ ፖሊሱ ተጠግቶ ‹‹ያ-ሀበሺ ያ-ኦሪያ›› ብሎ ሊይዘው ሆነ እንትኑን አውጥቶ መንገድ ላይ እየሸና ፖሊሱ ላይ ምላሱን ሲያወጣበት ዞሮ በሩጫ ተመለሰ፡፡ 40 ጂኒም ከመያዝ አመለጠ፡፡ ብቻ ታሪከ ብዙ ነው፡፡ አንድ ሰርግ ላይ ራሴ ያየሁትን ላካፍላችሁ፡፡ የኬክ መቁረሱ ስነ-ስርዓት ላይ ሁሉ ሞባይሉን አውጥቶ ሲቀርፅ እሱም ወንበር ላይ ቆሞ ከኋላ ኪሱ ቦርሳውን አውጥቶ የውሸት ቀረፃውን ቀጠለ፡፡ ሰዉ መጀመሪያውኑ ምን ይሰራል ብሎ ይጠብቀው ነበረ እና የሰርገኞቹን ትኩረት ሳይቀር ስቦ፣ በሳቅ ፀበል አጥምቆ ለተውሰነ ደቂቃ ፕሮግራም አስተጓጎለ፡፡

ከአርባ ጂኒ ውጭ ሌላም ሰው አለ፡፡ ቅፅል ስሙን ለራሱን 666 ብሎ የሚጠራ እና በዚህ ጥሩኝ የሚል፡፡ ባህር ውስጥ ሰምጨ 2 ቀን አድሬ ሳልሞት ወጣሁ የሚል ነው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ የለም፡፡ ይልቅ ከባህሩ ጋር በተያያዘ በአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ሊመዘገብ የሚገባው ታሪክ ያለው ሌላ ሰው አለ፡፡ ከሶማሊያ በጀልባ ከተነሱ ከአንድ ቀን በኋላ ማዕበል ባህሩን አናወጠው፡፡ ጀልባዋ ተፈረካክሳ ሰመጠች፡፡ ትረፍ ያለው ነፍስ የያዘ ታዕምረኛ ሰው ግን ከ16 ቀን በኋላ ጅቡቲ ጠረፍ ላይ አሳ አስጋሪዎች ቆዳው ተላልጦ ውሀ ነፍቶት በህይወት አገኙት፡፡ በወቅቱ ጅቡቲ ለረጅም ጊዜ ነዋሪ የነበረው ሰለሞን መርሻን አሁን የመን ነው፡፡ ይጠሩትና ይህ ልጅ ሀበሻ ነው በህይወት አለ ውሰድና አስታመው አሉት፡፡ አስታሞ አዳነው፡፡ ጀልባዋ የሰመጠችበትን ጊዜ ትልቅ መርከብ ላይ ሆነው ማዕበሉን ያሳለፉ ካሉት ቀን ጋር ልጁ የሚለውም ሲሰላ በትክክል 16 ቀን ባህር ውስጥ ነበር፡፡

ተስፋዬ ወለጋ ነው የሚሉት፡፡ የወለጋ ልጅ ስለሆነ ነው ተስፋዬ ወለጋ የሚሉት፡፡ የቀድሞ ባህር ኃይል አባል ነው፡፡ ልዩ ማስታወቂያ ከተማ ውስጥ በመለጠፍ ይታወቃል፡፡ ማስታወቂያው የሚለው ‹‹…በህገወጥ መንገድ ሰውን ወደ ሳዑዲ ለማስተላለፍ ምርጥ በሆነው ተስፋዬ ከሄዱ ጉዳት ይደርስብኛል ብለው አያስቡ፡፡ መመለስ ሲፈልጉም እንመልሳለን፣ ትዳር ከፈለጉም.. በዚህ ያህል ክፍያ… ››የሚል ነበር ተብሎ ሲወራ ሰምቻለሁ፤ እሱንም አነጋግሬዋለሁ፡፡ የመን ባለ ሀበሻ ዘንድ ብዙ ዘይገርም የሚያስብሉ ነገሮች አሉ፡፡

ሰሞኑን መንግስት ይውረድ ብለው የመን ውስጥ ችግር በነበረበት ሰዓት የታዘብኩትን ላካፍላችሁ፡፡ የመን ብዙ ስብጥርጥር የማይገባ ምስጢር፣ እርስ በእርሱ የሚምታታ ነገር ያለበት ሀገር ቢሆንም ለየመናዊያን ግን ነፀነት አለ፡፡ የፕሬዘዳንት አሊ አብደላ ሳላህ አህመር ወንድም እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጄኔራል አሊማሁሴን ጦሩን ይዘው በተቃዋሚነት ጎራ ገቡ፡፡ በልላ በኩል ሀሚድ አብደላ አልሀመር እና ሳዲቅ አብደላ አልሀመር አሳባ የሚባለው ቦታ ጦርነት ከመንግስት ጋር ከፈቱ፡፡ ሁሉም አንድ ቤተሰብ ናቸው፡፡ ሀየል የሚባለው አካባቢ ደግሞ ጀኔራል አሊማሁሴን ከመንግስት ጋር ጦርነት ከፈቱ… የሚገርመው ጦርነቱ በረድ ሲል የመንግስት እና የተቃዋሚው ወታደሮች አንድ ላይ ቁጭ ብለው ጫት ይቅማሉ፡፡ አብረው ይውላሉ፡፡ ትዕዛዝ ሲመጣ ሀያ በል ቻው ተባብለው ወደ ግዳጃቸው….ወደ በጥይት መነዳደላቸው… ሌላም አስገራሚ ነገር አለ፡፡ መንግስት የተቃዋሚ ወታደሮችን ደሞዝ እስካሁን እየከፈለ ነው፡፡ ደሞዝ እየከፈለ የሚዋጋ መንግስት….

ሁሉን እናውራው ብል ነገሬን፣ ማሳየት የፈለኩትን የወገኔን ችግር ወደ ቀልድ ይወስድብኛል፡፡ ለዛሬ በዚሁ ላብቃ እና አል-ቀረስ የሚባለውን ኢሰብአዊ ህይወት የሚገፋበትን ካምፕ እና ችግሩን ለማየት ወደዛ ሄጄ ስለነበር እመለስበታልሁ፡፡ በመጨረሻም አንድ አሳዛኝ ዜና ልናገር፡፡

የ 9ወር ልጇ እና ባሏ ላይ የፈላ ዘይት የደፋችው ኢትዮጵያዊ የመን ውስጥ ተፈረደባት

አንዲት አሚናት የተባለች ኢትዮጵያዊት ባሏን እና የዘጠኝ ወር ህፃን ልጇን የፈላ ዘይት ደፍታባቸው ተሰውራ ብትከርምም ተይዛ ፍርዷን ተቀበለች፡፡

ከአንድ ወር በፊት ባሏ እና ልጇ እንደተኙ ዘይት አፍልታ የደፋችባቸው አሚናት አናዶኝ ነው የሚል ምክንያት ሰጥታለች፡፡ አደጋው የደረሰበት አህመድ ያሲን ጁሜሪ የሚባለው ሆስፒታል ገብቶ ለሁለት ቀን እርዳታ ቢደረግለትም ራስ ቅሉ ላይ በደረሰው ከፍተኛ አደጋ ምክንያት ሊተርፍ አልቻለም፣ ሞተ፡፡ ትንሽ ልጃቸው አሁንም በከፍተኛ ህክምና ላይ ነው፡፡ ገና ከፍተኛ ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል የተባለ ሲሆን ፊቱ በመጎዳቱ ምክንያት ፐላስቲክ ሰርጅሪ መደረግ እንዳለበት የህክምና ባለሞያው ገልፀዋል፡፡

በአሰቃቂ ሁኔታ ዘይት አፍልታ የደፋችበትን ምክንያት ስትናገር ‹‹ እኔ ተቃጠልኩ አልቻልኩም፡፡ ሌላ ሴት ጋር እየሄደ አስቸገረኝ፡፡ አልፎ ተርፎ እጅ ከፍንጅ ያዝኩት›› ባይ ናት፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህ ለድርጊቷ በቂ ምክንያት እንዳልሆነ ገልፅዋል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ጠፍታ ከተሰወረችበት ቦታ ያሲያዛት ከበፊት ጀምሮ በውሽምነት ይዛው የነበረ የመናዊ መሆኑ ነው፡፡ ሲም ካርድ አዲስ ገዝታ ከእሱ ጋር ብቻ ለመገናኘት አስባ ስትደውልለት በድርጊቷ ተናዶ ስለነበር ሊያሲዛት ችሏል፡፡ ዝንጀሮ የራሷን መቀመጫ ሳታይ… የሚያስተርት ነው፡፡ ባሏ አጥቶ ቢሆን እንኳን የዘጠኝ ወር ህፃን አብሮ እንዲቃጠል የተደረገበት ምክንያት ግን አልተገለፀም፡፡

ፍ/ቤቱ ባለፈው 11/1/ 2012 ባዋለው ችሎት በሸሪዓ ህጉ መሰረት ህፃኑ አስራ ስምንት ዓመት ሞልቶት የመጨረሻው ፍርድ ልጁ ባለበት እስኪፈረድ ድረስ እስር ቤት እንድትቆይ ወስኗል፡፡ ከአስራስምንት ዓመት በኋላ ልጁ ባለበት የሚጠብቃት የሞት ፍርድ መሆኑን ያናገርኳቸው የህግ ባለሞያ የሸሪዓ ህጉን ጥቅሰው ነግረውኛል፡፡

ቸር እንሰንብት

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 17, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.