ሀበሻ በየመን (ክፍል 7)

እስረኛ ጠያቂዎች መጡ፡፡ የሽምሰዲን ሚስት ለመጡት ጠያቂዎች መታመሜን እንድትነግርልኝ ለመንኳት፡፡ ነገረቻቸው፡፡ ፖሊሶቹን ለምነው ጉርሻም ሰጥተው ገብተው አዩኝ፡፡ ትግርኛ ትንሽ..ትንሽ ስለምችል የሚያወሩትን እሰማለሁ፡፡ ይሄማ አጥንቱ ነው የቀረው ነፍስ የለውም ምኑን እንደክማለን አለች አንደኛዋ፡፡ ሌላኛዋ እኛ እንሞክር ማዳንም መግደልም የእሱ ነው ባይ ናት፡፡ ውስጤ አነባ ውስጤ ብቻ ሳይሆን አይኔም አንዠቀዠቀው፡፡ ተስማምተው እንዲያሳክሙኝ ፈለኩ፡፡ ምን ያደርጋል……ብዬ ነው ክፍል 6 ላይ ያቆመኩት፡፡

ሊያሳክሙኝ አለመስማማታቸው ፍርሃት ጫረብኝ፡፡ለምን አልፈራ? ያለኝ አማራጭ እነሱ ናቸው፡፡ ረጅም ሰዓት ተከራከሩ፡፡ ግዙፏ ሴትዮ አልተስማሙም፡፡ መጥፎ ተናግረው ተስፋ ያሰቆረጡኝም እሳቸው ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ማስተዋሉን ይስጣቸው፡፡ ቋንቋ አያውቅም ብለው መጥፎ ነገርም ሆነ ምስጢር የሚያወሩ ሰዎች ሁሌም ይገርሙኛል፡፡ ያን ቋንቋ እነሱ ብቻ በአደራ ተሰቷቸው ሌላው የሚያውቀው የማይመስላቸው ሰዎች ሞልተዋል፡፡ ቋንቋ መግባቢያ ስለሆነ ሌላውም ሊያውቀው ስለሚችል የሚያወሩትን መጠን ቢያደርጉት ያን ያህል ልቤን ባላደሙት ነበር፡፡በመጨረሻም አንደኛዋ ሩህ ሩህ አንጀት የተሰጣት በራሷ ወጪ አሳከመችኝ፡፡ዛሬ ያች ሴትዮ የህይወቴ ዋልታ ናት ቤተሰብ ነን፡፡ ለካ ችግሬ እንቅልፍ ማጣት ነውና ለሰባት ቀናት መርፌ ሲወጋኝ ሲወጋኝ ድብን ብዬ እየተኛሁ ተሻለኝ፡፡ ለሰባት ወር ከ14 ቀን እስር ቤት አሳልፌ ወጣሁ፡፡

እዛ በነበረኝ ቆይታ ያሳለፍኩት፣ ሀበሻዎች ላይ ሲደርስ ያየሁት አሁን ለማውራት ቦታው አይደለም፡፡አሁን ገብስ ገብሱን እናውራ..ያ-ስቃይ ራሱን የቻለ አንድ ታሪክ እና ሰቅጣጭ ምዕራፍ ነው፡፡ ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ ሰነዓ ከተማ ውስጥ ያለውም ስደተኛ ቢሆን ጣራውን ሰማይ ያደረገ እስር ቤት ውስጥ እንዳለ ነው የተረዳሁት፡፡ በእርግጥ የየመን መንግስት ለስደተኛው ምቹ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ችግሩ ኢኮኖሚያቸው እና የሰዉ ለውጭ ዜጋ በተለይ ለሀበሻ ያለው ጥላቻ ነው፡፡ ህይወት ሁሉ አርቲፊሻል ነው፡፡ ያውም አስጠሊታ አርቲፊሻል፡፡ ያልተብለጨለጨ የተሙለጨለጨ..የማያጓጓ አርቲፊሻል..ወገን ወገኑን ሲሸጥ የሚታይበት ጣራውን ሰማይ ያደረገ እስር ቤት፡፡ ከብዙ ነዋሪዎች ጋር ያደረኩት ቃለ-ምልልስም ቢሆን የሚያደላው ባዶ ኑሮ፣ የችግር ጎተራ ሆኖ መኖርን፣ ተስፋ ቢስነትን የሰነቀ ህይወት…

አስቡት ችግር ታሳልፍልኛለች የተባለች ልጅ ችግር የሚያበዛ፣ የቤተሰብ ቁጥር የሚጨምር ህፃን ይዛ ስትመለስ፡፡ ቤት ያለውን ሰው አፍ ማበሻ ፍለጋ ሄዳ አፍ ማበሻ የሚፈልግ ህፃን ለቤተሰቦቿ ይዛ የምትመለሰውን የችግርተኛ ቁጥር ያበዛችውን ቤት ይቁጠረው፡፡ በኮንትራት ስራ ተብሎ ከሚመጡት ውስጥ ከአዲስ አበባ የሳሪስን ያህል ሪከርድ የሚይዝ የለም፡፡ ዋናዋ ደላላ የሳሪስ ሰው በመሆኗ መሰለኝ፡፡ አንድ የሳሪስ ልጅ ጠቅልላ ስትገባ ልጅ ያልያዘ በሚለው የነገረችኝን ቀልድ ላካፍላቸሁ፡፡ ገና ኤርፖርት ስደርስ ቤተሰቦቼ ልጅ አልያዝሽም? አሉኝ፡፡ ግራ ገብቶኝ ‹‹የምን ልጅ›› አልኳቸው፡፡ ወዲያው ተደዋወሉ፡፡ ነገሩ የገባኝ ሰፈር ስደርስ ነው በእቅፍ አበባ የተቀበሉኝ መንገዱ ዳር ተሰልፈው ነበር፡፡ ከአረብ ሀገር ሻንጣ እንጂ ልጅ ይዛ አልመጣችም ተብሎ እንኳን ደስ ያለሽ..ባዩ ብዛት……

habesha in yemen 7

Habesha in yemen

By- Girum Teklehaimanot –

ይቺን ቀልድ ልብ መባል ያለባት ነች፡፡ ከቀልድነቷ በስተጀርባ ያደፍጠ፣ እውነታን ያዘለ መልእክት አለ፡፡ የሚበሉት ፍለጋ፣ ኑሮን ለማሸነፍ.. ብላ ልጅ ጨምራ የምትመጣውን ሴት ቁጥር በዋዛ ቤት ይቁጠረው ብሎ የሚታለፍ ብቻ አይደለም፡፡ ገንዘብ ይልካሉ፣ ችግር ይቀርፋሉ የተባሉ በግፍ አለያም ለገንዘብ በተደረገ የስሜት ፍልሚያ የተገኘ ልጅ የላኩ እዚህም ታቅፈው እያሳደጉ ያሉ እህቶቻችን ቁጥር ብዛት በጣም ያስደነግጣል፡፡ የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ወደው ገላቸውን መገበራቸው ራሱ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አይደሉም፡፡ የሰሩበትን፣ የለፉበትን ለወንድ አብልተው ልጅ ታቅፈው ካልሆነም ባዶ ቀርተው ሲታመሙ መታከሚያ አዋጡላቸው የሚባሉ ሞልተዋል፡፡ መታከሚያ አዋጡላቸው የሚባሉት ግን ለወንድ ያበሉት ብቻ አይደሉም፡፡ ሰርተው ያገኙትን ለቤተሰብ ሲልኩ ቆይተው መታከሚያ የሚያጡም አሉ፡፡ ..ብቻ ይሄ ነው ተብሎ ተቆጥሮ የማያልቅ ፍዳ የሞላበት ሕይወት ለመግፋት ሀገር ጥሎ መሰደድ ብኩንነት ነው፡፡ በመውለድና በጋብቻ በኩል ያለው ሲታሰብ ከሀገር ያስወጣቸው የባል ችግር እስኪመስል ያገኙትን ሀገር ዜጋ አግብተው የሰሩበትን እያበሉ የሚኖሩ ያጋጥማሉ፡፡ ስትለፋበት የኖረችውን ደግሳበት የሚበላው የሌለው ናይጄሪያዊ፣ ሶማሊያዊ..ህንድ…አረ! ጎበዝ ከትንሽ አመት በኋላ ምን የአፍሪካ ህብረት ብቻ የተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤትም ኢትዮጵያ እንዲሆን የምንጠይቅበት ሁኔታ እየተከሰተ ነው፡፡ ከአለም ያልወለድንለት ዜጋ ይኖር ይሆን? ቱቱ!!!…ቱቱ!.. ሴቶቻችን ማህፀናችሁ ይለምልም፡፡ አሜን በሉ!!

ከሌሎች ሁኔታዎች አንፃር፣ከነፃነት አንፃር.. ከሁሉም አረብ ሀገራት የመን የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ለሴቶቹ ስቃዩ፣ የሰሩበትን መከልከሉ፣ መታሰር፣ መደብደቡ፣ መደፈሩ…ይቀንሳል እንጂ የለም ማለት አይደለም፡፡ ሙስና የነገሰበት፣ ዘረኝነት የተንሰራፋበት ቦታ ቁጭ ብሎ መብት አለን ቢባል ውሸት ነው፡፡ ግን የመን ውስጥ ከፖሊስ ጋር አዩኝ አላዩኝ ድብብቆሽ የለም፡፡ ፖሊስ ሆኖ የሚያባርርህ ከእጅ ወደ አፍ የማይባል ኑሮው ነው፡፡ ተስፋ የሌለው ከፍ ዝቅ የማይል በድግግሞሽ የተሞላ ህይወት ይኖራል፡፡ እየኖሩ መኖርን የሚጠራጠሩበት የመን ውስጥ ለመኖር በባህር ያን ሁሉ ስቃይ መብላት ያሳዝናል፡፡ 10 እና 20 ዓመት ሰርተው ጠብ ያላለላቸው ሲታመሙ መታከሚያ አዋጡልኝ ተለምኖ የሚታከሙበት ህይወት..ሀገር ለመመለስ መሳፈሪያ ተለምኖ..እቁብ ተሰብስቦ..ተበድሮ የሚገባው ቁጥር ያመዝናል፡፡ ከእጅ አይሻል…ኑሮ ለመግፋት ክብርን አጥቶ ተዋርዶ በሰው ሀገር መንከራተት፡፡

እዚህ የመን ውስጥ በተለይ ለወንዶች ስራ የለም፡፡ /የለም እያሉ ስለሚያሳብቡ ነው የለም ያልኩት/ ፈፅሞ የለም ሳይሆን ችግር ነው፡፡ ክፍያው ምንም ነው፡፡ ወር ተሰርቶ 5 ቀን ቀለብ የማይሆን ነው ለወንዶች የሚከፈለው፡፡ ያውም ግማሹ ስራ ንቆ የሴት እጅ አይቶ፣ ጠብቆ ክብሩን ሸጦ ኗሪ ነው፡፡ ለሴቶች ከወንዶች የተሸለ ጥሩ ስለሚከፈል ሙጥኝ እነሱ ላይ የሚሉ ሞልተዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ሳስብ ‹‹የታዘሉ ወንዶች›› የሚል መጠሪያ ልሰጣቸው ግድ አለኝ፡፡ ሀሞተ ኮስታራ ሰርቶ የሰው እጅ ከመጠበቅ የወጣ ያልታዘለ፣ ሰው ላይ ሸክም ያልሆነ ወንድም ሞልቷል፡፡ ባይተርፈውም ካለው ላይ የሚረዳ፣ ሲቀፍሉት ለጫት የሚሰጥ ሰርቶ ያገኘም አለ፡፡ አብዛኛው ሀበሻ በሱስ የተጠመደ ለጫት፣ ለሲጋራ የእለት ወጪው ሲሯሯጥ ያገኘውን ሲለምን ይውላሉ፡፡/አራዳ ስለሆኑ በአራዲኛ ሲቀፍሉ ልበልላቸው?/ ሴት ወንዱ ጉንጫቸውን አሳብጠው ሲቅሙ፣ ሺሻ ለማጨስ ሲጋፉ… ሲጨቃጨቁ ማየት በየተሄደበት የተለመደ ነው፡፡ በሺሻ በኩል ሴቶች እህቶቻችን የበለጠውን ድርሻ ይዘው ኩሽናውን አፋቸው ውስጥ አርገው ጭስ ምገው ጭስ ሲተፉ የከሰል ባቡር የሚባለውን ይመስላሉ፡፡ ከሱሰኝነታቸው የተነሳ የሺሻ ማጨሻውን እቃ ይዘው በተጠሩበት ቦታ ሁሉ ይዞራሉ፡፡ ‹‹ጭሳማ›› ባንድ እላቸዋለሁ፡፡ ልክ መድረክ ሲያገኙ እቃቸውን አውጥተው ገጣጥመው እንደ ማይክራፎን አፋቸው ላይ ለጉመው የጭስ ዜማቸውን ያዜማሉ፡፡ ኑሮ አቃጥሏቸው መቃጠላቸውን ሳያውቁ ሌላ መቃጠያ የፈለጉ ናቸው፡፡ ማረራቸውን ግን ዘግይተው ያውቁታል፡፡ ሀገር መግቢያ፣ ማታከሚያ ሲያጡ ይባንናሉ፡፡

አልፎ አልፎ የሚበሉት አጥተው ቅልውጥ የሚዞሩ፣ ትራፊክ መብራት ላይ ቆመው የሚለምኑ፣ ሰርተው ሰርተው ሳምንት ስራ ቢፈቱ መንቀሳቀሻ የሌላቸው…ሞልተዋል፡፡ ለም ሀገር እየተባለች የምንክባት ሀገራችን ለምነቷ ለልጆቿ አልሆን ብሎ ግብርናቸውን ጥለው መሬታቸውን በባለ ብራም ኢንቨስተር ተነጥቀው ስደት የወጡ ጥቂት አይደሉም፡፡ አብዛኛው የሸዋ፣ የአርሲ፣ የባሌ፣ የሐረር ልጆች ኩብለላ ሰላም ማጣት እና ከላይ የጠቀስኩት ችግር ነው፡፡ እዚህም መጥተው አል-ቀረስ የተባለ ካምፕ ውስጥ ታጉረው እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ ማን አየላቸው? አል-ቀረስ ካምፕን ሁለተኛው ኦሽዊቲዝ ነው ማለት እችላለሁ፡፡

ከተማ ያለውንም ቢሆን ሁሉ የሚኖረውን ኑሮ አይና ‹‹ከሀገር ቤት ምን ያህል ይሻላል? ምንድን ነው ለውጡ?›› የሚል ጥያቄ ውስጤ ይላወሳል፡፡ መልስ ፍለጋ ስኳትን ‹‹ከኢትዮጵያ በምን ተሸሎ ነው እዚህ የምትደክሙት?›› የሚል ጥያቄ አነሳለሁ፡፡ አንዳንዶች ቴሌቪዥን፣ፍሪጅ፣ እና ሪሲቨር..መግዛታቸውን የህይወት ለውጥ አድርገውት ያዩታል፡፡ ቴሌቪዥን እና ፍሪጅ ቸግሮን ነው እንዴ ከሀገር የወጣነው? ሳስበው አንዳንዴ የምንፈልገውና የምንሰራውን ያላወቅነው ይመስለኛል፡፡ ይህ አብዛኛዎቻችን ላይ የሚታይ ችግር ነው፡፡ ሁለት አመት በኮንትራት ስቃይና እንግልታቸውን ሲያጣጥሙ ቆይተው ከሁለት ሺህ ዶላር በላይ አያገኙም፡፡ ያንንም ወደ ቤት የላኩት ከሌለ ነው፡፡ የሚገርመኝ ግን 85 ከመቶ የሚሆነው በዚሁ ሳንቲም አላስፈላጊ እቃ፣ ልብስ፣ ጌጣጌጥ..ቅብርጥሴ..ቡትቶ.. ሲሸምቱ ቆይተው በጣም ጥቂት ገንዘብ ይዘው ይገባሉ፡፡ የሚፈለገው ገንዘብ ሆኖ ሳለ…..ሁለት አመት የለፉበትን በቡትቶ መለወጥን አስቡት….

በድርቅ /ርሀብ/ ተጠቃ ለሚባል ህዝብ የራበው ኬክ ይመስል ጓዳ ጎድጓዳው ሁሉ ኬክ ቤት ሆኗል፡፡አብስሎ የሚሰጠው አጥቶ የተራበ ይመስል ሁሉ ቦታ ምግብ ቤትና ሆቴል ተከፍቶበታል፡፡የሚበላ ጠፍቶ በደርቅ ህዝብ አለቀ በሚባልበት ሀገር የመብላት ፈልጎት አጥቶ የተራበ እስኪመስል ነገር ጠገልብጧል፡፡ የመብላት ፍላጎት መክፈቻ አፒታይዘር በተገባበት መድኃኒት ቤት በገፍ ይገኛል፡፡ የሚስፈልገንንና የምንሰራውን ለይተን አለማወቅ አብሮን የከረመ መጥፎ አባዜ ነውና ልናስወግደው ይገባል፡፡

የመን ያለው ሁኔታ በተለይ UNHCR እና ቀይ መስቀል ስደተኞችን ያሰቀመጡበት ካምፐ ለኑሮ መመቸት አለመመቸት ብቻ አይደደለም የሚወለዱት ልጆችም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በምስሉ ላይ የምታዩዋቸው ህፃናት አልቀረስ የሚባል የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ያሉ በስቃይ የሚኖሩ ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ከሚበሉት ማጣት ጀምሮ ትምህርት እና ማንኛውም መሰረታዉ ነገር ባልተሟላበት ሁኔታ የሚያድጉ ልጆች ምን ሆነው ህይወታቸው ይቀጥላል? እዚህ ሀገር እንደመጣሁ እና የእስር ጊዜዬን ጨርሼ እንደወጣሁ በተደጋጋሚ ፖሊሶች እየተከታተሉ ያሰሩኝ ነበር፡፡ የስደተኞች ቢሮው /UNHCR/ ይህን የሚያደርገው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው አሉ እና አለ-ቀረስ ካምፕ ግባ ተባልኩ፡፡

የየመን ሁለተኛ ከተማ ወደ ሆነችው አደንም ተወሰድኩ፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን ኢንተርኔት ትጠቀማለህ ብለው የሌለ መረጃ ሰጥተው ላኩኝ፡፡ ይህን ያደረገችው አሁን ያለችው ፋጡማ የምትባል ፐሮቴክሽን ኦፊሰር እና ሳዲያ የምትባለው አሁን ከድታ አሜሪካ የገባች ትውልደ ኢትዮጵያዊ የስደተኛ ፋይል ይዛ ወጥታ ለኤምባሲ ስትሰጥ ተይዛ ከስራዋ ተባራ ድጋሚ የተመለሰች ሴት ናት፡፡ አደን ያለችው ፕሮቴክሽን ኦፊሰር ግልጹን ነገረችኝ ዱቄት እና ዘይት ተሰጥቶህ ነው አብስለህ የምትበላው እንኳን ኢንተርኔት ልትጠቀም አለችኝ፡፡ ለምን ዋሽተው ወደዚህ ካምፕ ሊልኩኝ እንደፈለጉ ስረዳ ለካ እዛ ውስጥ አማራም ሆነ የሌላ ብሄር ተወላጅ ሲገባ ይደበድባሉ፡፡ ክርስቲያን ሲሆን ደግሞ ካልሰለምክ፣ ካልሰገድክ ብለው ይገድላሉ፡፡ ከዛ በፊት ብዙ ሰው በዚህ መንገድ አስደብድበዋል፡፡ የሞቱም አሉ፡፡ UNHCR ይህን ቦታ የስደተኛው መቀጫ አድርጎ ነው ያለው፡፡ ሁኔታውን ካወኩ በኋላ ወደዚህ ካምፕ አልገባም በማለቴ እስከዛሬ ድረስ ምንም አይነት ሪሴትልመንት እንዳይሰጠኝ በቀይ ምልከት ተደረገብኝ፡፡

እዚህ የሰው ልጅ መሰቃያ ቦታ ስደተኛውም በዘር፣ በጎሳ፣ በእምነት፣ ተቧድኖ የሚባላበት ቦታ ለምን አልገባህም ተብዬ ዱረብል ሶሊሽን አታገኝም የተባልኩት ለምን ይሆን? ሞቴ የሚፈለግበት ምክንያት ይኖር ይሆን? ኤጭ ድከም ብሎኝ ነው እንዲህ ይህን ማሰቤ…እንግዲህ እኔም እንደ የመኑ ፕሬዘዳንት አሊ አብደላ ሳላህ 32 አመት የመንን ሙጥኝ ልል ነው ወይስ እንደ እሳቸው ለየመን ህዝብ ሰሰለቸው በሰላማዊ ሰልፍ ‹‹ይርሀል›› ይሂድልን ልባል ነው? ወይ ጉዴ!!! ወይ ወገን ማጣት……

በቀጣይ እንገናኛለን

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 7, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.