ሀበሻ በየመን ክፍል 6

(በግሩም ተክለሃይማኖት – የመን)

ባለፈው ፅሁፌ መጨረሻ ላይ ‹‹ከዚህ በፊት በዚህ ዙሪያ ያሰባሰብኩትን የቪዲዮ እና ፎቶ መረጃ በቪዲዮ መልክ አዘጋጅቼ ዩቱብ እና ፌስ ቡክ ላይ ለቅቄው ነበር ያላገኛችሁት ከሁለቱ መርጣችሁ ማየት ትችላላችሁ፡፡..›› የሚል መልዕክት ትቼ ነበር፡፡ ቦታውን ከመጠቆም ውጭ በዚህ ክፈቱት ማለት የግድ ነበረብኝ፡፡ ባለማድረጌ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ካላያችሁት አሁን  ክሊክ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡- የሰው ልጅ ፈተና……..

ይህን ፅሁፍ በመፅሀፍ መልክ ካዘጋጀሁት ላይ ቦጨቅ ድርጌ ለማስነበብ የወደድኩት ወድጄን አይደለም፡፡ አቅሙ ኖሮኝ መፅሐፉን እስከ አሳትመው ድረስ በስደት ከሚያልቁ ወገኖቼ አንድም ሁለትም ከሞት ማዳን ከቻልኩ ብዬ ነው፡፡ በሶማሊያ እና በጅቡቲ አድርገው ወደ የመን ሲሻገሩ ባህር ላይ በአመት የሚያልቁትን ከ2000 በላይ ወገን ቁጥር በአንድም ቢሆን መቀነስ ያስደስታል፡፡ ያ-ነውና አላማዬ እባክዎትን ስደት.. በተለይ ወደ የመን፣ሳዑዲ..በባህር ለመጓዝ ላሰቡ ሰዎች ከመንገር አልፈው ቪዲዮውን ያሳዩልኝ፡፡ አንድ ወገን ለማትረፍ እንረባረብ የዛሬ መልዕክቴ ነው፡፡ አሁን ወደ ቀጣዩ ፅሁፍ እናምራ…

ሶማሊያዊው የጀልባ ዘዋሪ /ናኩዳ/ አናቴን በዱላ ከበረቀሰኝ በኋላ ባህር ውስጥ የተነከረ ሻርፕ አናቴ ላይ ያዝኩበት..ውሀው ጨዋማ ስለሆነ ማቃጠሉን አትጠይቁኝ፡፡ ዝምታዬም ቢሆን ያመጣው ነገር የለም፡፡ አንደኛው የያዘውን ሀሺሺ እያቦነነ፣ ዱላውን እየነቀነቀ ወደ እኔ መጣ፡፡ ብዬ ነው ክፍል 5 ላይ ያቆምኩት ቀጠልኩ… አመጣጡ ሊማታ ነው የመሰለኝ፡፡ ውስጤ ተሸማቀቀ እሱ ግን የሚያጨሰውን ሀሺሽ ቁስሌ ላይ ተረኮሰልኝ፡፡ ቢያደፋፍረኝ ብዬ ተቀብዬ ያጨስኩት ሀሺሽ ቁስሌም ላይ ተተረኮሰ፡፡ ከብዙ ትግል በኋላ ደሙ ቆመልኝ፡፡ ተመስጌን!!!..ቀጣዩ መሬት የመርገጥ ጉጉት ነው፡፡ አቤት ያኔ የፀለይኩት ፀሎት….እስከዛሬ የያዘኝ እሱ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እንዲሁ ውሀ ብቻ እየጠጣሁ ያለ እንቅልፍ፣ ያለ እህል ወደ አርባ ሰዓት ያህል ተጓዝኩ፡፡ የያዝነውን አቡወለድ ሁለቴ ስቀምሰው ወዲያው ስለሚመለስ ስስ ፌስታል ፍለጋ ስለሆነ መብላቱን ትቼዋለሁ፡፡ በአርባኛው ሰዓት የጀልባው ጉዞ ሊጠናቀቅ ከአንድ ሰዓት በላይ ይቀረዋል፡፡ አቅጣጫ ስተዋል፡፡ ባይስቱ ኖሮ ከሰላሳ ስድስት እስከ ስላሳ ስምንት ሰዓት መጓዝ ያለብንን 40 ሰዓት ተጉዘን ቀሪ አይኖረንም ነበር፡፡ አንድ ጀልባ ወደ እኛ ስትከንፍ መጣች፡፡ ነጫጭ የለበሱ የየመን ባህር ሀይል አባላትን ጭናለች፡፡

ተኩስ ከፈቱ፡፡ ደነገጥን፡፡

ተኩሱ ወደ ሰማይ ነበር፡፡ ሶማሊያውያኑ አፀፋ አልሰጡም፡፡ የባህር ሀይሎቹ ተጠግተው አጅበው ወደ ዳር ሊያወጡን ጉዞ ተጀመረ፡፡ ሶማሊያዊያኑ ጀልባዋን መገልበጥ ፈልገዋል፡፡ ውሀ መሸፈጫው ስለማይሰራ የሚገባውን ውሀ በጀሪካን እየቀዱ ተቀባብለው የሚደፉትን አስቆሙዋቸው፡፡ ገብቶ ገብቶ በዛው እንድንሰምጥ፣ በአንድ በኩል ሆን ብለው ያጋድሉታል፡፡ ልቤም አብራ ታጋድላልች፡፡ እነሱ በጣም የሚመኩበት የዋና ልምድ አላቸው፡፡

ሴቶቹን አሰብኩ፡፡ እንዴት ሊሆኑ ነው? መሬት የሚባል ነገር አይታይም፡፡ እኔን ዘንግቼ ስለሰው አስባልሁ ራሴስ እንዴት ልሆን ነው? የፈለገ ዋና ብችል ከዚህ የመውጫ አቅም ኖሮኝ አልወጣም፡፡…አሁን ሲከፋኝ የልመና እሩምታዬን የምተኩስበትን አቅጣጫ አንጋጥጬ አየሁ፡፡ተጨማሪ ልመናዎች ላኩኝ፡፡

‹‹መቼም በዚህ ሰዓት እያየኸኝ ነው ያን ሁሉ ፈተና እንድወጣ አድርገህ ባህር ላይ አታስቀረኝም፡፡ ፈጣሪዬ ሆይ ፈርቻለሁ እና ከዚህ አውጣኝ፡፡ ብትፈልግ መላዕክትም…›› ድው…ድው..ድው…ተኩሱ ከሀሳብ ልመናዬ መንጥቆ አወጣኝ፡፡ አቋረጡኝ ያቋርጣቸውና..አቋራጮች፡፡ ነጭ የለበሱት የየመን ባህር ሀይሎች ጀልባቸውን አስጠግተው ወደእኛ ጀልባ ዘለው ወጡ፡፡ ሶማሊያውያኑ ሊገለብጡን እንዳሰቡ አውቀዋል፡፡ መሳሪያ ደግነው ጉዞ ተቀጠለ፡፡

በሆዴ ነው‹‹እል..እልልልል….›› አልኩኝ፡፡ በአፌማ አልደፍርም፡፡ ደግሞ ሁለተኛ ይበርቅሱኝ? ልመናዬን ሳልጨርስ ከተፍ አለልኝ፡፡ አምላክ..ማድረግ የሚችለውን ያደርጋል፡፡ ይህንኑ ማደረጉ…ነበር እና ቀና ብዬ ወደ ሰማይ አየሁ፡፡ ሆን ብለው ጀልባዋን ለማስመጥ ሙከራቸውን እንደቀጠሉ ባህር ኃይሎቹም እየተኮሱ፣ እየከለከሉ መሬት ልንረግጥ በግምት ሰባ ሜትር ያህል ሲቀረን ጀልባዋ ሙሉ ለሙሉ መስመጥ ጀመረች፡፡ እየዘለልን ወደባህር መግባት ግድ ሆነ፡፡ የባህር ሀይሎቹ ትናንሽ ጀልባዎች የሚችሉትን ያህል በተለይ ሴቶቹን ቅድሚያ እየሰጡ ማዳኑን ተያያዙት፡፡

በባህሩ ውሀ ሆዳቸው የተነፋ ሰምጠው የቀሩ ብዙ ናቸው፡፡ ትንሽዬ ዋና በመቻሌ የያዝኳትን ቦርሳ በጀርባዬ ይዤ ተፍጨረጨርኩ፡፡ ቦርሳዬ አመለጠኝ እና ለማዳን ስል ልሰምጥ ነበር፡፡ የተወሰነ ውሀ እንደጠጣሁ ራሴን ለማዳን ስታገል እጄን አፈፍ አድርጎ አንጠለጠለኝ፡፡ ጀልባቸው ላይ ወጣሁ፡፡ ህይወቴ ተረፈች እና መሬት ለመርገጥ በቃሁ፡፡

‹‹ተመስጌን አምላኬ!! ፀጋህ አይጓደል፡፡ ልመናዬን ሰምተኸኛል እና..›› እንባዬ መጣ፡፡መስመጣችንን እያለምኩ መሬት በመርገጤ እንዴት በደስታ አላነባ? ከዚህ በኋላ ወታደሮቹ የፈለጉትን ያድርጉኝ ብዬ ሰውነቴን ማሳረፍ ፈለኩ፡፡ ለ42 ሰዓታት ኩርምት ብዬ የተቀመጥኩበት እግሬ ውሀውን ለመቅዘፍ ባለመቻሉ በእጄ ብቻ ነበር የተጠቀምኩት፡፡ ርሀብ አጥወልውሎኛል፡፡ ውሀ ግን ብዙ ጠጥቻለሁ፡፡ አልፎ አልፎ ከርቀት ነጥብ አክላ ትታየን የነበረው ሁለተኛዋ ጀልባ ከቆይታ በኋላ በየመን ባህር ኃይሎች ታጅባ መጣች፡፡ ለመሬት ቀረብ ብሎ በመቆሙ ብዙም ጉዳት ሳይደርስባቸው መሬት ረገጡ፡፡ ጅብሪልን አየሁት፡፡ የትንሽ ቀን ጓደኛዬ ሳይሆን ወንድሜ መሰለኝ፡፡ ደስታው ውስጤን ናጠው፡፡ የሚገርመው ግን እሱም በአይኑ ሲፈልገኝ ነበር፡፡ ሲያየኝ ፈገግ ቢልም ፈገግታው በድካም የወየበ ነበር፡፡

አጠገቤ እንደደረሰ‹‹አልሀምድሊላህ ተጨንቄ ነበር የሰመጠው ጀልባ ውስጥ መስለኸኝ..››

‹‹አሀ!..የሰመጠውን ጀልባ አይታችሁታል?››

‹‹አዎ አይተነዋል፡፡›› አለኝ እንደዘበት፡፡ ለካ መከራም ሲበዛ ልብ ያደነድናል፡፡ ሰውነቴን ብርክ ይዞኛል፡፡ ፈፅሞ መቋቋም አልቻልኩም፡፡ ጅብሪልም ስለተረፈ ፈጣሪዬን አመሰገንኩት፡፡ የሞቱት ወንድሞቼ ግን በሀዘን ውስጤን አቆራመዱት፡፡‹‹ምነው ፈጣሪ መከራውን አበዛህብን እኛ ፍጡሮችህ አይደለንም? የእስከዛሬው አይበቃንም? በአዳም ሀጢያት ሞት እንደተፈረደብን በአባቶቻችን ሀጢያት ነው የምንቀጣው ወይስ ያላወቅነው ያጠፋነው፣ የምንቀጣበት ወንጀል አለን? መከራው ስቃዬ ስደቱ ማቆሚያ አልተበጀለትም? የዘውትር ዕጣ ፋንታችን ነውን?›› ስል ብዙ መልስ አልባ ጥያቄዎች ጠየኩት፡፡‹‹ለመከራ ተፈጥረን፣በመከራ ኖረን፣ በመከራ የምናልፈ አሳዛኝ ዜጎች…ምነው ዘነጋኸን?..››እንጃ አሁን ማስታወስ ያልቻልኩት ብዙ ጥያቄ ጠይቄ ብዙ ብሶት አሰምቻለሁ፡፡

ሰውነቴ ዛለ አልታዘዝህ አለኝ፡፡ እነሱ ደሞ አስነስተውን አሰለፉን፡፡ በሰልፉ መሰረት ቁጭ አደረጉን፡፡ አንድ ሳይቀር የያዝነውን እቃ ሁሉ ፈተሹን፡፡ እጅ ላይ ያለ ሰዓት ሳይቀር ያስፈታሉ፡፡ ገንዘብ የሶማሊያ ሽልንግ ሳይቀር ይወስዳሉ፡፡ ግን ምንም አይሰራላቸውም፡፡ የያዝኩትን ብር ቀስ አድርጌ አሸዋውን ጫር..ጫር አረኩና ቀበርኩት፡፡ ጊዜያዊ የቀብር ስነ-ስርዓቱን ፈፀምኩለት ልበል? ፈትሾኝ ሲያልፍ ቀስ ብዬ አውጥቼ ጫማዬ ውስጥ ከተትኩት፡፡ እነሰናይት የያዙትን በሶ አይተው ‹‹ሀሺሽ..ሀሺሽ..›› እያሉ ጮሁ፡፡ አረቢኛ የሚችሉት ልጆች አለመሆኑን እና ምግብ እንደሆነ ነገሯቸው፡፡ እየቀመሱም አሳዩዋቸው፡፡ እነሱም ቀመሱ፡፡ ብዙ ጊዜ በባህር የሚገቡ ሀሺሽ አመላላሾች መኖራቸውን ያወኩት ሰነዓ ከተማ ከገባሁ በኋላ በእነሱ አጠራር ሲጅናል መርከዚ የሚሉት ዋናው እስር ቤት እስረኛ ጥየቃ ስሄድ በሀሺሽ ሰበብ የታሰሩ ከሀያ አምስት በላይ ልጆች አግኝቻለሁ፡፡ ሞት ተፈርዶባቸው ወደ እድሜ ልክ የተቀየረላቸው 9 ልጆች አውቃለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይስጣቸው ከሞት ምን ይገኛል? እንኳን ማሩዋቸው፡፡

አካባቢውን ሲያስስ የቆየው የየመን ባህር ኋይሎች ጀልባ የሁለት ኢትዮጵያዊያንን ሬሳ ይዞ ተመለሰ፡፡ በዚህን ጊዜ ጀልባውን ሲዘውሩ ከነበሩት ሶማሊያዊያን አንዱ ተነስቶ ቆጠረንና ገና ስድስት ሰው እንደሚቀር ተናገረ፡፡

‹‹ከሁለቱ ጋር አጠቃላይ ስምንት ሰው ሞቷል ማለት ነው? ወይኔ..›› ውስጤ የጠየቀው ግን ያላወጣሁት ጥያቄ ነው፡፡ በምን ቋንቋ..ሬሳውን ስናይ ሁላችንም ተላቀስን፡፡ የሞቱት ለሁሉም ዘመድ ናቸው? ሲሉ መጠየቃቸውን አስተርጓሚዎች ነገሩን፡፡ የሁላችን ማልቀስ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ አሰልፈው ሊወስዱን ሲሉ ቋንቋ የሚያውቁት እንቀበር ሲሉ ለመኗቸው፡፡

ፈቀዱልን

የሁላችንም ድካም ወደ ብርታት የተቀየረ ይመስላል፡፡ በእጅ አሸዋውን መጫር ተጀመረ፡፡ሌሎች መቆፈሪያ የሚሆን ነገር ፍለጋ በየአቅጣጫው ባከኑ፡፡ በተገኘው ነገር ሁሉ የተቻለውን ያህል ተቆፈረ፡፡ አቤት ያለ ርብርብ!..ትብብር..ወደውጭ ማልቀስ የማይሆንልኝ እኔ እንኳን አሁን አሁን በሁሉ እያዘንኩ ነው መሰለኝ ተሳካልኝ፡፡ ይህ ያላሳዘነ፣ ይህ ያላስለቀሰ ምን ያስለቅሳል? ተንከራተን መጨረሻችን ይህ መሆኑ ነው ይበልጥ ያስለቀሰኝ፡፡ ተረባርበን ቀበርን፡፡ አቤት!! ደግሞ ለመቅበር አፈጣጠናችን!!!!!… ቀባሪ ስለሆንን ቀብር እንወዳለን ልበል? ከመረዳዳት ይልቅ፣ ታሞ ከመጠያየቅ ይልቅ፣ በደህና ቀን አብሮ ከመብላት ይልቅ ሲሞት ለመቅበር አንደኛ ነን፡፡

ቦታው በቀብር በመሞላቱ ነው መሰለኝ አጥንት ሁሉ እናገኝ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ቀይ መስቀልም ሆነ አይ ኦ ኤም ባወጡት መግለጫ ላይ በዓመት ከ2000 በላይ ሰው እዚህ ባህር ላይ እንደሚሞት ገልፀዋል፡፡

እንደገና አሰለፉንና ጉዞ ተጀመረ፡፡ ሰውነቴ አልታዘዝ አለኝ፡፡እግሬን መሬት ለመሬት እያንፏቀኩ ለመሄድ ሞከርኩ፡፡ ብዙም መጓዝ አልሆነልኝም፡፡ ምን እንደሆንኩ አላውቅም ተዝለፍልፌ ወደኩ፡፡ ልጆቹ እንደነገሩኝ ከሆነ ስወድቅ ድንጋዩ ልቤ ላይ መቶኛል፡፡ ለዛሬው የልብ ህመሜ መነሻ ይሁን አይሁን ግን የማውቀው የለም፡፡ በሰዓቱ ያላቸው አማራጭ በመሆኑ እኔን ደግፈው መሄድም የእነሱ እዳ ሆነ፡፡ የወሰዱን ወደ ቀይ መስቀል ጊቢ ነው፡፡ ሰራተኞቹ አናስገባም ስላሉ ከጊቢ ውጭ ተደረደርን፡፡ ደግፈው የያዙኝ ልጆች ሙጥኝ ብዬ የያዝኳት ቦርሳዬን አንተርሰው አስተኙኝ፡፡ ረሴን ያወኩት ግን ከስንት ሰዓት በኋላ እንደሆን ባላውቅም ቀዝቃዛ የጠርሙስ ጭማቂ ሲያጠጡኝ ነው፡፡ የሰጡኝን ሩዝ ለመብላት ጉሮሮዬ የጠበበ ሁሉ መሰለኝ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መተንፈስ አቅቶኛል፡፡ ቦርሳዬን ለማዳን ስታገል የተጎነጨሁት የባህር ውሀ ጥሩ ስሜት አልሰጠኝም፡፡ እንደ አሳ ሆዴ ውስጥ ይዋኛል፡፡ግልገሎቹ ገብተው ይሆን እንዴ?

አቅም አጣሁ፡፡ ድካም ተሰማኝ፡፡ ለ42 ሰዓት ስንጓዝ ለሰከንድ እንቅልፍ በአይኔ አልዞረም፡፡ሜዳው ላይ ጋደም እንዳልኩ እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡ለምን ያህል ሰዓት እንደተኛሁ ባላውቅም፡፡ ወታደሮቹ አንስተው መኪና ላይ ሊጭኑኝ ሲታገሉ ነቃሁ፡፡ የቀይ መስቀል ሰዎች ትላልቅ የጭነት መኪና አምጥተው እየጫኑ ማይፋ የሚባለው የሶማሊያዊያን መጠለያ ካምፕ እየወሰዱ ነው፡፡ የመጨረሻው መኪና ላይ የመጨረሻው ተጫኝ ነኝ፡፡ለምን ያህል ሰዓት፣ በምን አይነት ሁኔታ እንደተጓዝን ምንም አይነት ትዝታ የለኝም፡፡

‹‹ማይፋ›› የሚባለው ካምፕ ስንደርስ መጨላለሙን አውቃለሁ፡፡ ከዛ በኋላ ራሴን ያገኘሁት ህክምና ጣቢያ ውስጥ ጉልኮስ ተሰክቶልኝ ነው፡፡ አጠገቤ አንድ ጉንጩን በጫት ወጥቆ የማር ስልቻ ያስመሰለ ሰው ቆሟል፡፡

‹‹ጋዜጠኛ ነኝ ነው ያልከው? ማስረጃ አለህ?›› አለኝ ጥርት ባለ አማርኛ ‹‹አሀ ቀባጥሬያለሁ ማለት ነው?›› አልኩ በውስጤ፡፡

‹‹አዎ››

‹‹ጉልኮሱን ጨርስና አናግረኝ›› ከእሺ ሌላ ምን እላለሁ?የተሰካልኝን ጉሉኮስ ስጨርስ ላናግረው ብሄድ ራትህን ብላና ተመለስ ብሎ የሰጠኝን ካርድ ነገር ይዤ ምግብ ወደ ሚታደልበት ቦታ ሄድኩ፡፡ሩዝ፣ ወጥ፣ዳቦ እና ሻይ ተሰጠኝ፡፡ ብርታት ነገር ቢሰማኝም ትንሽ ረሀብ ቢጤ ሸንቆጥ ስላደረገኝ ምግብ የምመርጥበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ቢኖር ኖሮ ሲያዩት የሚያስጠላ፣ የሚዘጋ ስለሆን አልነካውም ነበር፡፡ ሩዙ ከድንች፣ከዱባ እና ባሚያ ወጥ ጋር ፅዳት በሌለው ሁኔታ ተደባልቆ የተጨማለቀ ነው፡፡

የሚፈልግ ገላውን ይታጠብ አሉ፡፡ ይሄ መታደል ነው፡፡ሮጨ መጀመሪያ ተሰለፍኩኝ፡፡የአለም ሁሉ ቆሻሻ እላዬ ላይ የተከመረ የመሰለኝ ገና ጀልባ ላይ ስንወጣ ነው፡፡ታጥቤ ሰወጣ ያ አናገረኝ ያለኝ ሰው ጋር ሄድኩኝ፡፡ መፍትሄም የለው ጉራውን ሊነዛ ነው የጠራኝ፡፡

ይልቅ እሱ ራሱን ክቦ ክቦ ጣራ ሊያስነካ ሲጣጣር ያ- ሁለት እግሩን አሞት በሰው ታዝሎ የሚሄደውን ልጅን አስታወስኩት፡፡ ወጣሁና መፈለግ ጀመርኩ፡፡

አየሁት የሚል አጣሁ፡፡

የተኙትንም እየቀሰቀስኩ አየሁ፡፡ እንዲያውም ለምን ቀሰቀስከን በሚል ከሁለት ልጆች ጋር ተጣላሁ፡፡ በመጨረሻም ጅብሪልን አግኝቼው አገዘኝ፡፡ ግን ልጁ የለም፡፡ ጅብሪል ግን እስካሁንም የመን ነው ያለው፡፡ ከጅብሪል ጋር አጠገብ ለአጠገብ አንጥፈን ተኛን፡፡ እንቅልፍ ግን ከእኔ ዘንድ መጠጋትን አልመረጠም፡፡ በልመና ሲጠጋኝም  ባህሩ ላይ ከሞት ጋር ትግል ሲያደርጉ ያኋቸው ሰዎች የጣር ጩኸት፣ እግሩን የሚያመው ልጅ አድነኝ እያለኝ ብቅ ጥልቅ ሲል ይታየኝ ጀመር፡፡ ጩኸቴን በረጅሙ ለቀቁትና ተነሳሁ፡፡አብዛኛዎቹ ነቁ ረበሽከን ብለውም ወቀሱኝ፡፡ የእኔን መረበሽ ማን ይረዳልኝ? በተከታታይ ለ13 ቀናት እንቅልፍ በአይኔ መዞር አልቻለም፡፡ ገና ጋደም ስል ይታዩኛል፡፡መተኛት አልችልም፡፡ ለካ በመሀል እንቅልፍ ማጣት ጭንቅላቴን ቀየር አድረጎታል፡፡ ፎቶ ተነስቼ ወደ ሀገሬ አልመለስም ብዬ ስለበጠበጥኩ ቅጣት ተብሎ ፀሀይ መሞቂያ ጣራ የሌለው ጊቢ ነገር ውስጥ ነበር የታሰርኩት፡፡ ምን ያህል ቀን ራሴን እንዳላወኩ አላውቅም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ እስረኛ የሚጠይቁ ቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚሰጡ የተዋህዶ ልጆች ተረባረቡልኝ፡፡ በዚህን ወቅት ከጎኔ ሳትለይ በማስታመምም ሆን የፈለኩትን ሁሉ በማሟላት ሸዋዬ የምትባል ልጅ አሁንም በዛው ቤተክርስቲያን ውስጥ ዘማሪ ሆና የምታገለግል የምረሳት አይደለችም፡፡

እንቅልፍ ማጣት ራሴን ካሳተኝ በሁለተኛው ይሁን በሶስተኛው ቀን ዝናብ እየዘነበ ነበር ይመስለኛል፡፡ በባዶ እግሬ ጊቢው ውስጥ እዞራለሁ፡፡ ተዝለፍልፌ ወደኩ፡፡ ማን ያስታመኝ? አንድ ህንዳዊ አንድ ሸምሰዲን የሚባል የድሬደዋ ልጅ ከነሚስቱ ነበሩ፡፡ሊያስታምሙኝ አልፈቀዱም፡፡ ለሽንት መነሳት ሁሉ አቃጠኝ፡፡ ለቁርስ እና ለእራት ሻይ የሚሰጡት በፉል ቆርቆሮ /ጣሳ/ ስለሆነ እየደፋሁት እሱ ላይ እሸናለሁ፡፡

እስረኛ ጠያቂዎች መጡ፡፡ የሽምሰዲን ሚስት ለመጡት ጠያቂዎች መታመሜን እንድትነግርልኝ ለመንኳት፡፡ ነገረቻቸው፡፡ ፖሊሶቹን ለምነው ጉርሻም ሰጥተው ገብተው አዩኝ፡፡ ትግርኛ ትንሽ..ትንሽ ስለምችል የሚያወሩትን እሰማለሁ፡፡ ይሄማ አጥንቱ ነው የቀረው ነፍስ የለውም ምኑን እንደክማለን አለች አንደኛዋ፡፡ ሌላኛዋ እኛ እንሞክር ማዳንም መግደልም የእሱ ነው ባይ ናት፡፡ ውስጤ አነባ ውስጤ ብቻ ሳይሆን አይኔም አንዠቀዠቀው፡፡ ተስማምተው እንዲያሳክሙኝ ፈለኩ፡፡ ምን ያደርጋል…… በቀጣዩ እመለስበታለሁ፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 24, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.